ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26 /2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።


 

ድሬደዋ ከተማ በ24 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ60 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። 

ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች የተሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። 

የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ መሪነቱን ያጠናክራል። ከተከታዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ከፍ ያደርጋል። 

በሌላኛው መርሐ ግብር ይርጋጨፌ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ጋር ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ይርጋጨፌ ቡና በ17 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሃዋሳ ከተማ በ46 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

በ23ኛ ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2 ለ 1 የተሸነፈው ይርጋጨፌ ቡና ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል። ከወራጅ ቀጠና ስፍራ መራቅ የሚያስችለውን ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።

በአንጻሩ ሃዋሳ ከተማ በ23ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል። ቡድኑ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ እና ወደ አራተኛ ደረጃ በድጋሚ ለመመለስ ይፋለማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም