ቀጥታ፡

የጣና ሐይቅ ተቀድቶ የማያልቅ የልማት ምንጭ፤ የማይደበዝዝ የውበት ጮራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018(ኢዜአ) የጣና ሐይቅ ተቀድቶ የማያልቅ የልማት ምንጭ፤ የማይደበዝዝ የውበት ጮራ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳስታወቁት ለባሕር ዳርና ለአካባቢው ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ይዞ የመጣውን ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ዛሬ መርቀን ለአገልግሎት ከፍተናል።

ዳርቻ የለሽ የተፈጥሮ ውበት ከሰው ልጆች ትጋት ጋር ሲደመር ምን ውጤት እንደሚገኝ ባሕር ዳር ማሳያ ናት ሲሉም ተናግረዋል።


 

ባሕር ዳር በኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ እና በዓለም ትልቁ ወንዝ የሚገናኙባት ከተማ ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያዋ ፈጣሪ የሰውን መንፈስ በነፍስም በሥጋም ለማደስ የፈጠረው አካባቢ ነው በወዲያ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት አለ ብለዋል በመልዕክታቸው።

ተሻግሮ የጎንደር ፋሲለደስ ደረቱን ነፍቶ ይታያል መነሻ በወዲህ በገበታ ለሀገር ኢኒሼቲቭ ተጠንስሶ በአቶ ካሣሁን(ቢአይካ) የተገነባው የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ይገኛል፤ በመሐል ዓባይና ጣና ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

ዛሬ የመረቅነው የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ለከተማዋና ለሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተጨማሪ የውበት እና የልማት ከፍታ ነው ብለዋል።

መንግሥት ለቱሪዝም መዳረሻዎች የሰጠው ትኩረት ምን ውጤት እንዳመጣ በገሐድ የሚነበብበት ፕሮጀክት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአካባቢውን የቱሪዝም መሥመርና ሠንሠለት የሚያጠናክር ማረፊያና መዳረሻም ነው።

 


ሪዞርቱ
ዘመናዊ እና ቅንጡ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ሱቆች አምፊ ቴአትር እና መሰል መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ፣ ጣናን ተንተርሶ የተሠራ ሪዞርት ነውም ብለዋለ።

በባሕር ዳር ኢንቨስት ለማድረግ ሥራ የጀመሩና መሬት የተረከቡ ኢንቨስተሮች እንደ ፈለገ ግዮን ሥራዎቻቸውን በፍጥነት እንዲፈጽሙ አደራ እንላለን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም