በአማራ ክልል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ጸጋዎችን ለዓለም የሚያስተዋውቁ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እውን እየሆኑ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ጸጋዎችን ለዓለም የሚያስተዋውቁ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እውን እየሆኑ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የአማራ ክልልን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ጸጋዎች ለዓለም የሚያስተዋውቁ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ እውን እየሆነ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩመህ በገበታ ለሀገር ኢኒሼቲቭ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን መነሻ በማድረግ በባህር ዳር ከተማ ጣና ዳርቻ በባለሀብቱ ካሳሁን ምስጋናው የተገነባውን ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
በመርኃ ግብሩ የአማራ ክልል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ባለሀብቶችና የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በባህር ዳር ከተማ በጣና ሐይቅ ደቡባዊ ዳርቻ ላይ የተገነባው ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ገበታ ለሀገር" እቅድ መሰረት በሐይቁ ሌላኛው አቅጣጫ ከሚገኘው የጎርጎራ ብርሃን (ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት) ጋር በመቀናጀት የጣናን የቱሪዝም ቀጣና ለማነቃቃት የታለመ ነው።
ይሄው በአራት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው ሪዞርት፤ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ ታውቋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ የሚገኙት የቱሪዝም መዳረሻዎች የክልሉን ውበት ከመግለጽ ባለፈ፣ እስካሁን በበቂ ሁኔታ ያልታወቁ ጸጋዎችን ይፋ እያደረጉ ይገኛሉ።
ቀደም ሲል የተገነባው የጎርጎራ ፕሮጀክት፣ ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት እና ሌሎች ግንባታዎች የክልሉን ውበትና የኢትዮጵያን የብልጽግና ከፍታ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አዲሱ ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት የጣና ሐይቅን ደህንነት በጠበቀ መልኩ የተገነባ፣ የጥራትና የምቾት መለኪያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አመልክተዋል።
ሪዞርቱ በታላቁ ወንዝ ስም የተሰየመ የጎብኚዎች መዳረሻ መሆኑን አመልክተው፤ ክልሉ ከቱሪዝም ዘርፍ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በመንግሥትና በግለሰቦች በጋራ የመሥራት ባህል የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ እውን እየሆነ መሆኑንና በቀጣይም መሰል የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ለትውልድ የሚተርፉና ሀገርን የሚያስከብሩ ሥራዎች መሥራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።