የገበታ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያን በላባችን ሀገር መገንባት እንደምንችል ማሳያ ናቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የገበታ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያን በላባችን ሀገር መገንባት እንደምንችል ማሳያ ናቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የገበታ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያን በላባችን ሀገር መገንባት እንደምንችል ማሳያ ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገበታ ለሀገር ኢኒሼቲቭ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን መነሻ በማድረግ በባህር ዳር ከተማ ጣና ዳርቻ በባለሀብቱ ካሳሁን ምስጋናው የተገነባውን ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የአማራ ክልልና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ባለሀብቶችና የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የሪዞርቱ መገንባት ለክልሉና ለሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የቱሪዝም ዘርፍ መጠናከር ተጨማሪ አቅም እንደሆነ ገልጸዋል።
በጎርጎራና በፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርቶች መካከል የሚፈጠረው ትስስር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጎብኚዎች ከባህር ዳር ወደ ጎርጎራ፣ ጎንደር፣ ራስ ዳሽን፣ ላሊበላና ትግራይ ክልል የሚያደርጉትን ጉዞ በማቀናጀት የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
የገበታ ፕሮጀክቶች ዓላማቸው ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋና ውበት ገልጣ ለዓለም እንድታሳይ ማድረግ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ግብ አሁን ላይ ፍሬ እያፈራ ነው ብለዋል።
አክለውም ኢትዮጵያውያን በደማችን ሀገር መጠበቅ እንደቻልን ሁሉ በላባችንም ሀገር ማልማት እንደምንችል በእነዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እያሳየን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ባህር ዳር በትልቅ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ ልማት ምህዋር ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ የዓባይ አዲሱ ድልድይ በጎንደርና በጎጃም መካከል ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከማጠናከሩ ባለፈ ራሱን የቻለ የቱሪስት መዳረሻ መሆኑን ገልጸዋል።
እየተጠናቀቀ የሚገኘው የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ዓለምአቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም ባለው ደረጃ መገንባቱን ጠቁመዋል።
አዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ዓለምአቀፍ በረራዎችንና በርካታ መንገደኞችን በማስተናገድ ለአካባቢው ዕድገት የላቀ መሆኑንም አክለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ኢኒሼቲቮች ላይ በንቃት ለተሳተፉ ባለሀብቶች ምስጋና አቅርበዋል።
ባህር ዳር ሰላም መሆኗን በመግለጽም፣ ዳያስፖራዎች የወሰዱትን መሬት እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።