ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ረገድ የበኩሏን ሚና እየተወጣች ነው  

‎አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ረገድ የበኩሏን ሚና እየተወጣች እንደምትገኝ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ። 

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ለ13ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 556 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የኮሌጁ ተመራቂዎች በጠቅላላ ሕክምና፣ በስፔሻላይዜሽንና በተለያዩ የጤና ሳይንስ ዘርፎች የሰለጠኑ መሆናቸው ተገልጿል። 

ከተመራቂዎቹ መካከል 204ቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ 14ቱ ደግሞ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ናቸው።


 

ዶክተር መቅደስ ዳባ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ። 

ዘርፉ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ ለሕክምናው ወሳኝ የሆኑ ዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂዎችና የምርመራ መሣሪያዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ብቁ የሕክምና የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክተው፤ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እያከናወነ ያለው ተግባር ለአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአህጉሪቷ የጤና ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ከ400 በላይ አፍሪካውያን የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠን መቻሏንም የጤና ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።

የኮሌጁ ፕሮቮስት ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ኮሌጁ ባለፉት 13 ዓመታት በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ ባለሙያዎችን አፍርቷል። 


 

ተቋሙ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኮሌጁ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በተለያዩ የጤና ተቋማት ተሰማርተው የኅብረተሰቡን የጤና ችግር በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ዶክተር ሙሉቀን አስታውቀዋል። 

ከተመራቂዎች መካከል የወርቅ ተሸላሚው ዶክተር ይከበር ቴዎድሮስ እንደገለጸው፤ ባገኘው እውቀት ያስተማረውን ማኅበረሰብ በትጋትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነው።

ዶክተር ህሊና ዳዊት በቆይታዋ በንድፈ ሐሳብና በተግባር የተደገፈ በቂ እውቀት ማግኘቷን ገልጻለች።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም