ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አምራቾች ከማምረት ባሻገር የአፍሪካ ገበያን መጠቀም የሚያስችል የንግድ ትስስር መፍጠር አለባቸው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አምራቾች ከማምረት ባለፈ የአፍሪካን ገበያ መጠቀም የሚያስችል የንግድ ትስስር መፍጠር እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚያዝያ 25 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።

ለአራተኛ ጊዜ "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተዘጋጀው ኤክስፖ ላይ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምኅረት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበልን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለፉት አራት ዓመታት በውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል።

አምራቾችና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተዋንያን የኢኮኖሚ አርበኝነትን ሊላበሱ እንደሚገባ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም ሌብነትና ኮንትሮባንድን በመጸየፍ እውነተኛ የኢኮኖሚ አርበኛ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አምራቾች በአገር ውስጥ የማምረት ተግባር ላይ ብቻ ተወስነው የሚቆዩበት ጊዜ አብቅቶ፣ አሁን ወደ አፍሪካ ሰፊ ገበያ የሚገቡበት ወቅት ላይ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገለጹት።

እስካሁን “አምርቱ” በሚል ማበረታቻ ሲደረግ የነበረው ጥረት አሁን አምራቾች የአህጉሪቱን የንግድ ዕድሎች ለመቀላቀል እንዲወጡና እንዲሰማሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

አምራቾች አቅም ካላቸው በግል፣ ካልሆነም በጋራ በመጣመር አሊያም ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ኩባንያዎችን በመመስረት ወደ አፍሪካ አገራት ዘልቆ መግባት አገራዊ ግዴታቸው ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በራሷ ትልቅ ገበያ ያላት አገር መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን ሰፊ የንግድ ዕድል ለመጠቀም አምራቾች ከማምረት ባለፈ ገበያውን ለመቆጣጠር መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

አንዱ አምራች እዚህ እያመረተ ሌላው ደግሞ በውጭ አገራት እያከፋፈለ የአፍሪካን የንግድ ሰንሰለት መቆጣጠር ለነገ የማይባል የቤት ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ትልቅ ራዕይ ከግብ እንዲደርስም መንግሥት ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ለማድረግ የራሱን የቤት ሥራ በአግባቡ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።


 

በሀገር ውስጥ በማምረት 96 የምርት ዓይነቶችን መተካት እንደሚቻል መለየቱን ጠቁመው፤ እነዚህን የኢንዱስትሪ ባለሀብቶች የምርት ዓይነቶች በማወቅና በአገር ውስጥ በማምረት ከውጭ እንዳይገቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በቅርቡም የኢትዮጵያን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ መሸፈን የሚያስችል የሴራሚክ ፋብሪካዎች ለምረቃ እንደሚበቁ አስታውቀው፤በዚህም በማምረት ክብራችንን፣ ነጻነታችንን እና እድገታችንን ማፋጠን እንችላለን ሲሉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የ10 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንደምታስመዘግብ ገልጸው፤ በግብርና፣ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና ከሁሉም በላይ በቴክኖሎጂ ዘርፎች አስደናቂ የሆነ ፈጣን እድገት ላይ መሆኗን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ገበያም ማቅረብ እየቻለች መሆኗን ገልጸዋል።

ለአብነት በመከላከያ ምርቶች ረገድም ቀደም ሲል ከውጭ ይገቡ የነበሩ በርካታ የምርት ዓይነቶችን በአገር ውስጥ ከመተካት ባሻገር ከስድስት በላይ ለሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶችን መሸጥ መጀመሩን ተናግረዋል።

በመከላከያ፣በልብስ እና በመድኃኒት ምርቶች ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን፤ እነዚህን ማምረት የሚያስችሉ ማሽነሪዎችን ጭምር ማምረትና መሸጥ ስንጀምር ሀገራችን በተሟላ ቁመና ላይ ትገኛለች ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም