በለውጡ መንግስት የክልሉ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በለውጡ መንግስት የክልሉ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እያደገ መጥቷል
ሰመራ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦በለውጡ መንግስት የክልሉ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እያደገ መጥቷል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ገለጹ።
''ከዳር እስከ መሃል ውጤታማ የብዝሃ ዘርፍ'' በሚል መሪ ሐሳብ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በመተባበር ያዘጋጁት የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
በመድረኩ በመገኘት ውይይቱን ያስጀመሩት በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ፤ ኢትዮጵያ በእኩልነት የምንኖርባት የሁላችንም የጋራ ቤት ሆናለች ብለዋል።
በተለይም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድሎች መመዝገባቸውን ገልጸው የአግላይነት ፖለቲካ ተወግዶ ህዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እኩል የመወሰን መብትን ተጎናፅፈዋል ብለዋል።
በለውጡ ዓመታት በአፋር ክልል በተለያዩ ብዝሃ ዘርፎች ውጤታማ የሚባሉ መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው የአፋር ክልል የለውጡ ዕውን መሆንን ተከትሎ ፖለቲካዊ ድሎችን መጎናፀፍ ችሏል ብለዋል።
እውነተኛ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ በመደረጉም የክልሉ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ከለውጡ ማግስት አንስቶ በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ያሉት ደግሞ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር ናቸው።
በክልሉ ለዘመናት ጥቅም ላይ ሳይውሉ የቆዩ ወንዞችን በአግባቡ በመጠቀም የእርሻ ስራዎችን በማስፋፋት እንደ ቆላ ስንዴ፣ ሙዝ፣ ፓፓያና ሸንኩርት በስፋት በማምረት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በአካባቢው እምብዛም የማይዘወተሩ አዳዲስ አዝዕርቶችን የማላመድ ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ በእንስሳት ሀብቱ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ አበረታች ለውጦች መኖራቸውን ጠቅሰው ክልሉ ከጨው ሀብት ዘርፉ በተገቢው መጠቀም መቻሉንም አብራርተዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ በበኩላቸው፤ በጤናና በትምህርት መስኮች የተሻሉ ስራዎች በመሰራታቸውና ተደራሽነትን ማስፋት በመቻሉ ተጠቃሚነት ማደጉን ገልጸዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።