የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና እያበረከተ ይገኛል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ አራተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ አስጀምረዋል።
በኤክስፖ መክፈቻ ሥነ ስነ ሥርዓት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምኅረት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ በመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ ያላትን አምራች የሰው ኃይል ተጠቅማ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ረገድ እየታዩ ያሉ ተጨባጭ ውጤቶች፣ ሀገሪቷ ከጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ምንም የሚያስቆማት ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው።
በመደመር እሳቤ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመደመር መንግሥት ኢንዱስትሪን የሚመለከተው ለሀገር ከሚኖረው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ባሻገር የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ፣ ከጥገኝነት ተላቆ ራስን ከመቻል እና ከሀገራዊ ክብር ጋር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ያረጋገጡት።
ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የምንሰጠው ትኩረት ጫናዎችን ተቋቁሞ ቀጣይነት ባለው መንገድ የምትበለጽግ ሀገርን መፍጠር እንድንችል ትልቅ ሚና ይጫወታል ሲሉም ገልጸዋል።
መንግሥት የኢንዱስትሪው መስክ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተውን ሚና ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ፣ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በማውጣት፣ ለዘርፉ ተዋናዮች ምቹ የስራ ምኅዳርን በመፍጠር ረገድ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በመስኩ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በየደረጃው የሚያጋጥማቸውን ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ለመፍታት የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል በማቋቋም፣ አምራቾችን በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የማገዝ ተግባር በስፋት ሲከናወን መቆየቱንም አንስተዋል።
በለውጡ ዓመታት በተሰራውም ስራ የሀገሪቷን የማምረት አቅም ማሳደግ መቻሉን የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ፤ በዚህም ተኪ ምርቶች የማምረት አቅም እንዲያድግና የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ እንዲሻሻል አድርጓል ነው ያሉት።
የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ማኅበረሰቡ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቱንም አብራርተዋል።
የኤክስፖው መዘጋጀት ከሚኖረው ጠቀሜታዎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸው ትስስር ለማጠናከር፣ የልምድ ልውውጥ ለማጎልበት፣ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር የሚያስችሉ የምርምር እና የቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በቀጣይም በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ባለፉት አራት ዓመታት የመጡትን ተጨባጭ ለውጦች ለማስቀጠል፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከፋይናንስና ከመሰረተ ልማት አኳያ ያለባቸውን ማነቆዎች የመፍታት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የገጠር ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ተግባር ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም አመላክተዋል።