የቴክኖሎጂ እምርታ -ሌላው የኢትዮጵያ ከፍታ ጉዞ አመላካች - ኢዜአ አማርኛ
የቴክኖሎጂ እምርታ -ሌላው የኢትዮጵያ ከፍታ ጉዞ አመላካች
የቴክኖሎጂ እምርታ -ሌላው የኢትዮጵያ ከፍታ ጉዞ አመላካች
በሙሴ መለሰ
በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታየው የቴክኖሎጂ ለውጥ ወደ ዘመናዊው የዲጂታል ምህዳር እያሸጋገራት ይገኛል።የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የመሰረተ ልማት እና የተቋማት ግንባታ ስራዎች ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በምታደርገው ጉዞ ውስጥ የሚጠቀሱ ዋንኛ ስራዎች ናቸው።
ለውጡን ተከትሎ መንግስት "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" የተሰኘውን ስትራቴጂ በመቅረጽ የዲጂታላይዜሽን ስራውን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ምሰሶ አድርጎታል።
የለውጡ መንግስት ስልጣን ከያዘ በኋላ ቴክኖሎጂን እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምሰሶ በመቁጠር "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" የተሰኘውን አጠቃላይ ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ተግባር ገባ።ይህ ስትራቴጂ የሀገሪቱን የዲጂታል ጉዞ ከመሰረቱ የለወጠ ሲሆን፣የመጀመሪያው ትልቅ እርምጃም የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ ነበር።
የቴሌኮም ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መደረጉ የሳፋሪኮም ወደ ኢትዮጵያ መግባትና የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶችን የማዘመን ስራ የኢንተርኔት ተደራሽነት እንዲሰፋ ምክንያት ሆኗል።በተለይም የአምስተኛ ትውልድ (5G) ቴክኖሎጂ አገልግሎት መጀመር ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንድትሆን አስችሏታል።
የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ለውጡ የፋይናንስ ዘርፉ ላይ ውጤት አምጥቷል።እንደ ቴሌብር (telebirr) ያሉ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ያለ ምንም የባንክ ሂሳብ በስልካቸው ብቻ ግብይት እንዲፈጽሙ በማድረግ፣ ሀገሪቱ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንድትሸጋገር ትልቅ መደላድል ፈጥረዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ረገድ የተመዘገቡት ስኬቶችም የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ አድማስ ይበልጥ አስፍተውታል።
የኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት መቋቋም ሀገሪቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን ራዕይ ለዓለም ያሳየችበት አጋጣሚ ነው።ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት በጤናው ዘርፍ የካንሰር ህመምንና የሳምባ በሽታዎችን ቀድሞ መለየት የሚያስችሉ የኤአይ ውጤቶችን አበልጽጓል። በግብርናውም ረገድ የአፈርን ለምነትና የሰብል በሽታን በቴክኖሎጂ የመለየት ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ ይህም በምግብ ዋስትና ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ሌላው ትልቅ ስኬት የሀገር በቀል ቋንቋዎችን በዲጂታል ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ የተሰሩ የቋንቋ ፕሮሰሲንግ (NLP) ስራዎች ናቸው። ይህም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ውስጥ እንዲካተቱና ለተጠቃሚው ምቹ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
የፋይዳ (Fayda) ብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን መረጃ በአንድ ማዕከል በመሰብሰብ፣ ለባንክ፣ ለጤናና ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች አስተማማኝ መሠረት ጥሏል።
በአሁኑ ወቅት ዜጎች እንደ ፓስፖርት ማደስ፣ የንግድ ፈቃድ ማውጣትና ግብር መክፈል ያሉ አገልግሎቶችን ከቤታቸው ሆነው በኢንተርኔት ማከናወን መቻላቸው የለውጡ ፍሬያማነት ማሳያ ነው።የሳይንስ ሙዚየምም የወጣቶችን የፈጠራ አቅም የሚያሳይና የሀገሪቱን ቴክኖሎጂ የሚደግፍ ትልቅ አቅም ሆኗል።የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በቅርቡ መጠናቀቁ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2025 ስትራቴጂው መጠናቀቁን ተከትሎ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ታህሳስ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት ደግሞ የስትራቴጂው ቁልፍ መሰረታዊ ትልሞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ም ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን መሰረት በማድረግ መዘጋጀቱን አንስተዋል።ትልሞቹ እንዲሳኩም በተለይ የህዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋት ላይ ትልቅ ስራ እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ይህም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰው ተኮር ሆኖ የዜጎችን ኑሮ እንዲያሻሽል ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በአጠቃላይ በዲጂታል ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ስራዎች የመደመር መንግስት በቀለለ ቢሮክራሲ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን እውን ለማድረግ ከያዘው ግብ ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እንዲሳካም ሁሉም በትብብር መስራት እንዳለበት ነው ጥሪ ያቀረቡት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዲጂታል 2030ን ይፋ ሲያደርጉ የነበረው ትልቁ መልዕክት ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዓለም ተመልካች ሳይሆን ተሳታፊና መሪ ትሆናለች የሚል ነው።
ስትራቴጂው በዋናነት"የፋይዳ" ዲጂታል መታወቂያን ከሁሉም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ጋር በማቀናጀት፣ ለዜጎች ቀልጣፋ አሰራርን መፍጠር፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዲጂታል ስራ እድሎችን ለወጣቶች ማመቻቸት እና ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል (Innovation Hub) አድርጎ መገንባትን እንደ ዋነኛ ግብ አስቀምጧል።
ይህም ሁሉን አቀፍ የኢንተርኔት ተደራሽነትን በማረጋገጥ፣ የመንግስት አገልግሎቶችን መቶ በመቶ ወረቀት አልባ በማድረግ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) በግብርና፣ በጤናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ በስፋት በመተግበር የምርታማነት አብዮት መፍጠርን ያለመ ነው።
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ የጀመረችው ስራ በአህጉራዊ ደረጃ ያለውን ተቀባይነትና የተሰጣትን ትልቅ ኃላፊነት የሚያሳይ ነው።ኢትዮጵያ አሁን ላይ የደረሰችበት የቴክኖሎጂ ከፍታ፣ ሀገሪቱን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ተፎካካሪ ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ምንጭ እንድትሆንም እያደረጋት ይገኛል።
በዚህ ረገድም የቀጣዩ ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ስኬትም ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባና በቴክኖሎጂ የበለጸገች ሀገር የማድረግ ራዕይን ለማሳካት እና ለሀገራዊ ብልጽግና እንደ ቁልፍ ሞተር ሆኖ ያገለግላል።