በማምረት ክብራችንን እና ነፃነታችንን በማስከበር ዕድገትን ማምጣት ይጠበቅብናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በማምረት ክብራችንን እና ነፃነታችንን በማስከበር ዕድገትን ማምጣት ይጠበቅብናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያዊያን በማምረት ክብራችንንና ነፃነታችንን በማስከበር ዕድገትን ማምጣት ይጠበቅብናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚያዝያ 25 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።
ለአራተኛ ጊዜ "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተዘጋጀው ኤክስፖ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምኅረት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ማምረት ሉዓላዊነትን ያጎናፅፋል፣ አለማምረት ደግሞ ታሪክን ያጎድፋል ብለዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ ፀጋዎቿን አልምታ ባለመጠቀሟ በዓለም አቀፋዊ ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ ተግዳሮት ገጥሟት እንደነበር አውስተው፤ በዚህም በሁሉም መስክ ማምረት የተሟላ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ አበክሮ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አብዛኛውን ፍላጎቱን በገቢ ምርት ላይ ያደረገ ሀገር ነፃና ሉዓላዊ ነኝ ሊል አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ አምርታ የተሟላ ሉዓላዊነት እንድትጎናጸፍ በኅብረትና በአንድነት በመሥራት ለልጆቻችን ነፃና የተሟላ ሉዓላዊነት የተጎናጸፈችዋን ኢትዮጵያ ዕውን ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የዛሬ አራት ዓመት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርታማነት በጥራት፣ በደረጃና በዓይነት እያደገ መምጣቱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ዘንድሮ የኢትዮጵያን የ10 ነጥብ 2 ዕድገት ለማረጋገጥም የኢንዱስትሪና የኢትዮጵያ ታምርት የሚፈጥሩት ጥምረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተዋል።
ከዓመታት በፊት የወጪ ንግድ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለመሻገር ሲንገዳገድ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ቢሊዮን ዶላር በማሳካት ታላቅ ድል እንደሚሆን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ዘርፍም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር የነበረው የአራት ነጥብ ሰባት ዕድገት አሁን ላይ 10 ነጥብ 7 ዕድገት ማስመዝገቡን አስረድተዋል።
ባለፉት አራት ዓመታትም ከውጭ ይገባ የነበረን የ14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በሀገር ውስጥ መተካት እንደተቻለም አስታውቀዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የቆዩ 993 ኢንዱስትሪዎችም መልሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አንስተዋል።
ባለፉት አራት ዓመታትም 3 ሺህ 680 አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን መቀላቀል እንደቻሉ ጠቅሰዋል።
በኢንዱስትሪ ዘርፍ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በተኪ ምርትና በወጪ ንግድ ዕድገት ገንቢ ሚና እየተወጡ ለሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮች ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ካላመረትን ክብርና ነፃነታችንን መጎናጸፍ አንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር ለዘርፉ ዕድገት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
አራተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በመጎብኘት ሊያተርፉበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።