ቀጥታ፡

ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በተሰጠው ልዩ ትኩረት የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ ነው

ደሴ፤ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በሰጠው ልዩ ትኩረት የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የደሴ ከተማ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ አመለከቱ።

"ብልጽግና ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት" በሚል መልእክት ሴቶች ብቻ የተሳተፉበት የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍና የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ዛሬ በደሴ ከተማ ተካሄዷል።


 

በወቅቱም በብልጽግና ፓርቲ የከተማዋ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ እንደገለፁት፤ ፓርቲው ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በሰጠው ልዩ ትኩረት የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ ነው።

ፓርቲው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተግባር እየሰራ ያለውን ስራ ሴቶች ተገንዝበው በሰልፍ መደገፋቸው በቀጣይ ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ በከተማው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቅስቀሳና ድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተገኙት መካከል ወይዘሮ ደህንነት ጫኔ እንደገለፁት፣ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተማው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።


 

በተለይም ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በተሰጠው ትኩረት የሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ማደግ በመቻሉ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተናል ብለዋል።

ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ላቀች አበበ በበኩላቸው፣ የብልጽግና ፓርቲ በሌማት ትሩፋት፣ ለአቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታና በሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።


 

የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ፓርቲውን በመደገፍ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

የጤና አገልግሎቱን በማዘመን፣በተማሪዎች ምገባ፣ በኮሪደር ልማትና በሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሴቶች በተግባር ተጠቃሚ መሆን ችለናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሶፊያ መሀመድ ናቸው።


 

በደሴ ከተማ ከልማት ስራዎች በተጓዳኝ ገበያውን ለማረጋጋት፣ በቱሪዝምና በሌሎችም አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ ዛሬ እዚህ ተገኝተናል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የደሴ ከተማ አመራሮች፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ደሴን የሚወክሉ ተመራጮችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም