ቀጥታ፡

አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦አዲስ አበባን እንደስሟ ውብና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን የከተማዋ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታወቀ።

መንግስት ካለፉት የለውጥ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሀብቶችን በመግለጥ፣ በርካታ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በነባሮቹ ላይም እሴት የመጨመር ስራዎችን አከናውኗል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች እንዲሁም የኤምባሲዎች መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባን ስሟን የሚመጥን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እና ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።


 

ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠው ትኩረት እና በተሰሩ የልማት ስራዎች አዲስ አበባ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል። 

ለአብነትም የእንጦጦ፣ አራዳ፣  ወዳጅነት፣ አንድነት ፓርኮች እንዲሁም በከተማዋ መሃልና ዙሪያ ያሉ ተፋሰስ ወንዞችን እና የኮሪደር መሰረተ-ልማቶችን ጨምሮ ሌሎች የአረንጓዴ ልማት ስፍራዎች ይጠቀሳሉ።

በዚህም ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች በመጠቀም ረገድ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃንና የአካባቢ ዘላቂነትን ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞ ትልልቅ ስራዎች ተሰርተዋል። 

ይህም አዲስ አበባን ልዩ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን፤ ባህልን፣ ታሪክንና ተፈጥሮን አጣምራ የያዘች ልዩ መስህብ አድርጓታል።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በለውጡ ዓመታት በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ አስደናቂ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

በመዲናዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥራትና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ግንባታዎች ተከናውነው ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል። 

በመሆኑም በከተማዋ ያሉ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን በማልማት፣ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በማስተዋወቅና የኢኮኖሚ ምንጭ በማድረግ በኩል ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉም ተናግረዋል።

ከለውጡ ወዲህ በመዲናዋ የተሰሩት የልማት ስራዎች የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች እንዲፈጠሩ ማስቻሉን ገልጸው፤ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል። 

ለውጡን ተከትሎም በኮሪደር ልማት ከተማዋን ለኑሮ ምቹ፣ ፅዱና ማራኪ በማድረግ፤ ስሉጥ የእግረኛ፣ የብስክሌትና የተሽከርካሪ መንገዶችን ጨምሮ አረንጓዴ መናፈሻዎች በመገንባታቸው በዘርፉ ላይ እድገት መመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም