ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የወባ በሽታን ለመከላከል በተከናወኑ ስራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦በድሬዳዋ አስተዳደር ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት በሽታውን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የጤና ባለሙያዎችና የዘርፉ አመራሮች ገለጹ።

ድሬዳዋ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧና በሞቃታማ የአየር ንብረቷ ምክንያት ለወባ በሽታ ተጋላጭ ከሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዷ መሆኗ ይታወቃል። 

ይህንን ተጋላጭነት ለመቀነስና የህዝቡን ጤና ለመጠበቅም የተለያዩ የመከላከያ ስራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን በዚህም ውጤቶች መመዝገባቸው ተገልጿል።

በሳቢያን ወረዳ የጎሮ ጤና ጣቢያ ስራ አስኪያጅ የጤና መኮንን እንዳለማው እርቅይሁን እንዳሉት፤ ለወባ በሽታ መንስኤ የሆኑ የትንኝ መራቢያ አካባቢዎች በተቀናጀ መንገድ በማዳረቅና ኬሚካል በመርጨት ወባን በተጨባጭ መከላከል ተችሏል።


 

በተለይም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች  ለህብረተሰቡ ተገቢውን የመከላከያ ትምህርት በመስጠት በመከላከሉ ስራ ላይ በባለቤትነት በማሳተፍ የተከናወኑት ተግባራት ፍሬያማ ሆነዋል ብለዋል።

ነዋሪው ጊቢውንና አካባቢውን በማፅዳት፣ ውሃ ያቆሩ አካባቢዎችን በማፋሰስና በማዳረቅ እያከናወነ የሚገኘው ስራ  በአብነት የሚጠቀስ መሆኑን በመግለፅ።

ከመከላከሉ ጎን ለጎን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በወባ በሽታ ለተያዙ 2ሺህ 900 ሰዎች ተገቢውን ህክምና በመስጠት የማዳን ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

አምናና ዘንድሮ ወባን ለመከላከልና ለማጥፋት የተሰሩ ስራዎች በወባ የሚያዙ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ ማስቻሉንም ገልጸዋል።

የመልካ ጀብዱ ወረዳ  ጤና ጣቢያ ባለሙያ ቤተልሄም እንዳለ በበኩላቸው፤  ዘንድሮ ወባን ለመከላከልና ለማጥፋት የተከናወኑ ተግባራት የበሽታውን ስርጭት እንዲገታ አስችሏል።

በተለይም የትንኝ መራቢያ ወንዞችና የኢንዱስትሪ አካባቢዎች ላይ ኬሚካል ርጭት በማካሄድ አካባቢዎችን ከስጋት ነፃ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ለታመሙትም አስፈላጊው ህክምና እየተሰጠ መሆኑን በማስታወስ አንድም በወባ የተያዘ ታካሚ በጤና ጣቢያው እንደሌለም ገልጸዋል።

ወባን ለመከላከል በተሰሩ ስራዎች የመጡ ለውጦችን ይበልጥ በማሳደግ ከወባ ነፃ የሆነ መልካጀብዱን ዕውን ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው፤ የወባ በሽታን በመከላከልም ሆነ በየጤና ተቋማት በወባ ለተያዘ  ሰው እየተሰጠ የሚገኘው ህክምና አበረታች ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል እያደረገ የሚገኘው ተሳትፎ እየተጠናከረ መምጣቱ እና በሁሉም ጤና ተቋማት የፀረ ወባ መድኃኒት እና ፈጣን መመርመሪያ ኪት እንዲሟላ መደረጉ የበሽታውን ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ አስችሏል ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በወባ በሽታ ህይወቱ ያለፈ አንድም ነዋሪ አለመኖሩን ጠቅሰው ይህን ውጤታማ ጉዞ በማስቀጠልና ድሬዳዋን ከወባ ነፃ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም