ቀጥታ፡

የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር

ክልሎች፤ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፡-የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር

በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮች በወፍ በረር ሲቃኙ ይህንን ይመስላሉ!!!

👉ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነቡትን የቶዮ ሶላር ኢነርጂ ምዕራፍ ሁለት፣ የኦሪጂን እና የሉሚንቴክ የሶላር ፋብሪካዎችን እንዲሁም የኤች.ዜድ ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካን በይፋ መርቀዋል። እነዚህ የሶላር ፋብሪካዎች በጋራ በዓመት 11.3 ጊጋ ዋት ንጹሕ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን፣ የኤች.ዜድ ጋዝ ፋብሪካ ደግሞ በዓመት 900 ቶን ኦክስጅን፣ 40,000 ቶን ናይትሮጅን እና 7 ቶን ሃይድሮጅን ለገበያ ያቀርባል።

‎ይህ ክንውን የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል ልማት ለማፋጠን፣ የኢነርጂ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ዘላቂ፣ የማይበገር ሁለንተናዊ እድገት ዕውን ለማድረግ የተነደፈውን ስትራቴጂ ለማሳካት ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል።

👉እንቁላልን ሳይበላሽ ለሁለት ዓመት የማቆየት ልምምድ

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ የዶሮ እንቁላል ሳይበላሽ ለሁለት ዓመት ያህል ማቆየት የሚያስችል ቴክኖሎጂን ወደ ተግባር ለማስገባት ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል። በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ሕክምናና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ማስተዋል ብርሃን፤ ዩኒቨርሲቲው የእንቁላል ምርት ብክነትና ብልሽትን ለማስቀረት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም እንቁላልን እስከ ሁለት ዓመት ያለ ምንም ብልሽት ማቆየት የሚያስችለውን ቴክኖሎጂን የማላመድና የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ቴክኖሎጂው በአንድ ሊትር ውሃ ውስጥ 30 ግራም የኖራ አፈር ወይም ላይም ስቶን ጨምሮ በማዋሃድ እስከ 12 እንቁላሎችን ሳይበላሽ የሚያስቀምጥ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ ተመራጭ ነው ያሉት።  

ይህም እስካሁን ባለው አንድ ትኩስ እንቁላል ሳይበላሽ መቆየት የሚችለው እስከ ሁለት ሳምንት መሆኑን ጠቁመው ቴክኖሎጂው ይሄን ችግር በመሰረታዊነት የሚቀይር ነው።፡ ቴክኖሎጂውን በስፋት በማስተዋወቅና በማላመድ ረገድም ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን በመስጠት ችግር ፈቺነቱን የማሳየት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። 

👉የአፋር ጥጥ ተስፋ ሰጪ ፀጋ!

የአፋር ክልል የበርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ነው፤ ሆኖም እነዚህን እምቅ ሀብቶች ወደ ልማት በመቀየር ከፀጋዎቹ ተቋዳሽ ለመሆን ሳይቻል ለረጅም ተቆይቷል። አሁን ግን ከፀጋዎቹ አንዱ የሆነውን ተፈጥሯዊ ጥጥ (Organic Cotton) ለማምረት ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። 

በሰመራ በተካሄደ የውይይት መድረክም በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳምሶን አሰፋ፤ የአፋር ክልል ጥጥን በመስኖ ማልማት የሚቻልበት አቅም ያለው በመሆኑ ልማቱን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል። በሀገራችን የጥጥ ልማትን ለማስፋፋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፤ ባለፈው የምርት ዘመን እንደ ሀገር በስድስት ክልሎች 110 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ መልማቱን ተናግረዋል።በዚህም 79 ሺህ ሜትሮክ ቶን የተዳመጠ ጥጥ በማምረት ለኢንደስትሪዎች ማቅረብ  እንደተቻለ ነው የገለፁት።

👉የሸማቹ ሸክም ይቀላል!

የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን “ወደ ቀበሌ መድረስ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ስድስት ከተሞች ሀገር አቀፍ የህብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ ሲያካሄድ የህብረት ስራ ማህበራት ከእንግዲህ የሸማቹን ሸክም ሊያቀሉ ይገባል የሚል ሀሳብ ተነስቷል።

በሀዋሳው በተካሔደው የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት በተለያዩ መስኮች የበለጸገችና ህብረ ብሔራዊት ሀገር ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን አንስተዋል። በተከናወኑ ተግባራትም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን አክለዋል።

የመንግስትን፣ የግሉ ዘርፍንና የዜጎችን የካፒታል አቅምና ዕውቀትን ደምረው የያዙት የህብረት ስራ ማህበራት ግብርናውን በማሻገር የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት በመቀየር ረገድ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልፀው የፋይናንስ አቅርቦት ችግርን በመፍታትና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር የሸማቹን ህብረተሰብ ሸክም ያቀላሉ ተብሎ እንደሚታመንም አስረድተዋል።

👉ምርምር ለቀጣናዊ ትስስር

በጅማ ዩኒቨርሲቲ "ቀጠናዊ ሰላምና ትብብር ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ባለችበት ቀጣና የሚታዩ ፍላጎቶችን ለማሟላትና ተግዳሮቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ጥናቶች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተነስቷል።

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጦሽኔ ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር በሚደረግ ጥረት የትምህርት ተቋማቱ የጥናትና ምርምር ድጋፍ ከፍተኛ ሚና አለው ያሉ ሲሆን ለዚህም ተቋማቱ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያሳድጉ እና ማህበራዊ ፈተናዎችን ለመፍታት የሚያግዙ የፖሊሲ መነሻ ሀሳቦችን በጥናትና ምርምር እንዲያፈልቁ  አሳስበዋል።

የሚወጡ ጥናቶች በቀጣናው በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሊሆኑ እንደሚገባ የተጠቀሰ ሲሆን ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራን በመተግበር እያከናወነች ያለችው ተግባር በተመክሮነት ቀርቦ አድናቆትን አስገኝቶላታል። 

👉ሻይ ቅጠል 

አሁን አሁን አርሶ አደሩ በተለያዩ ኢንሼቲቮች በሚከናወኑ የግብርና ልማት ትግበራዎች ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ይገኛል። በርካታ አርሶ አደሮች በሻይ ቅጠል ልማት ኢንሼቲቭ በመሰማራት ገቢን ከማሳደግ ባለፈ ለሌሎችም ሰፊ የስራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ። በጅማ ዞን የሻይ ቅጠል ልማትን ከማስፋፋት ባለፈ የበያ ትስስር የመፍጠርና  ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለፋብሪካ ለማቅረብ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑም ተገልጿል።

የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ቲጃኒ ተማም፤ በዞኑ የሻይ ቅጠል ልማትን በኢኒሼቲቨን መልክ በመተግበር   የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ  ተጠቃሚነት  ከማሳደግ  ባለፈ  ለበርካቶች የስራ ዕድል  እየተፈጠረ ነው። ዘንድሮም ስራውን ለማስቀጠል በተመረጡ 6 ወረዳዎች በመጪው ክረምት የሚተከሉ 50 ሚሊዮን ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን ህዝብን በማሳተፍም ወደ 2 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬትን ለመሸፈንም ታስቧል።

ጥቅሙ የገባቸው አርሶ አደሮችም የሰብል ልማቱን ለጊዜው ተወት በማድረግ በሻይ ቅጠል ልማት ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ ይናገራሉ። በዞኑ  የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ አርሶ አደር ሲራጅ ሼክ ከድር በሻይ ቅጠል ልማት ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ወዲህ ገቢያቸው መጨመሩን ተናግረዋል። አርሶ አደር  ሱልጣን አባሞጋ በበኩላቸው ተሰማርተውበት ከነበረው የሰብል ልማት ወደ ሻይ ቅጠል ልማት በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል። የአካባቢ ፀጋን ተገንዝቦ ወደ ስራ መግባት ተጠቃሚነትን እንደሚያመጣ ማሳያ ሊሆን ይችላል። 

👉ተስፋዎች

ከሳምንቱ አንኳር ጉዳዮች መካከል በሆሳዕና ከተማ የተካሄደው የሞዴል ኢንተርፕራይዞች ደረጃ ሽግግር እውቅና መርሃ ግብር ይጠቀሳል። "የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ለእመርታዊ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ የተከናወነው የዕውቅና መድረክ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት ነው የተካሄደው። እሳቸው እንደገለፁት፤ ኢንተርፕራይዞቹ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩ ነው። በክልሉ በገጠርና በከተማ በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፍ ከ25 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ መስኮች መሰማራታቸው የተገለፀ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ በጥቃቅንና በአነስተኛ ደረጃ የሚገኙ 4 ሺህ 948 ኢንተርፕራይዞችን የማሸጋገርና 495 ሞዴል ኢንተርፕራይዞችን የመለየት ስራ መሰራቱም እንዲሁ። ከኢንተርፕራይዝ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሸጋገሩ አምራቾች እንደተናገሩት ሽግግሩ ስራቸውን በተሻለ ሁኔታ ለመከወን እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል። 

👉ትምህርትና አርብቶ አደሩ

የወፍ በረር ቅኝታችንን ስንቀጥል ጋምቤላ እንደርሳለን፤ በሳምንቱ በጋምቤላ ከተማ በተካሄደ መድረክም የአርብቶ አደሩን የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውም ተመልክቷል። በለውጡ ዓመታት የአርብቶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ውጤት መመዝገባቸውም እንዲሁ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት የአርብቶ አደሩን የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የገዘፈ መሆኑም በመድረኩ መገለፁን ቅኝታችን ዳሶታል።

👉ልወቅሽ ኢትዮጵያ

ሁነቶቹን ጠቅለል አድርጎ የዳሰሰው ቅኝታችን ደግሞ በስድስት ከተሞች ለማካሄድ ዕቅድ የተያዘለትና እስካሁን በጅማ፣ በሀዋሳና በደብረ ብርሃን ከተሞች የተካሄደው የ"ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ታላቁ ሩጫ" ከተሞቹን ከማስተዋወቅ የዘለለ ፋይዳውን በመርሃ ግብሩ ላይ በተላለፉ መልዕክቶቹ አሳይቷል። ለአብነት በጅማ የተካሄደው ‘ፖሊዮን በጋራ እናጥፋ’ የሚለውን የጤና ጉዳይን ያነሳ ነበር። በአዳማ ከተማ የተከናወነው ሁነት ደግሞ በመኪና ውድድር ታጅቦ የተከናወነና የቱሪዝም መስህቦችን ማስተዋወቅን ታላሚ ያደረገ ነበር።  ‘’ለሀዋሳ ከፍታ እንሮጣለን’’ በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው ሁነትም ከጅማና አዳማው ሁነት የተለየ እሳቤንም ሆነ መልዕክትን አልያዘም። ሁሉም ሁነቶች ከዋነኞቹ አምስት ምጣኔ ሃብታዊ አምዶች መካከል አንዱ የሆነውን ቱሪዝም ልማት በማጠናከር የማህበረሰቡን የዘርፉ ተጠቃሚነት ማላቅን ታሳቢ ማድረጋቸውን መመልከት ተችሏል።  

ቅኝቶቻችን በወፍ በረር ይህንን ይመስላሉ!! የሳምንት ሰው ይበለን!!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም