በጠቅላላ ምርጫው የፖሊሲ አማራጮቻችንን በተለያዩ ሚዲያዎች ሳንገደብ ማቅረብ ችለናል - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላላ ምርጫው የፖሊሲ አማራጮቻችንን በተለያዩ ሚዲያዎች ሳንገደብ ማቅረብ ችለናል
ሰመራ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ያለ ምንም ገደብ ለህዝብ ማቅረብ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ (አነግፓ) ሊቀ መንበርና የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሃንፈሬ አሊሚራህ ገለጹ።
ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦቻቸውንና ማኒፌስቶዋቸውን ለህዝብ እንዲያስተዋውቁ የመገናኛ ብዙኃን እኩል የአየር ሰዓትና ሰፊ መድረክ መመደባቸው ይታወቃል።
ይህም ሚዲያዎች ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድ ያላቸውን ሚና በተግባር እያሳዩ መሆኑን አመላካች ሆኗል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ(አነግፓ) ሊቀ መንበር አቶ ሃንፈሬ አሊሚራህ፤ በዘንድሮው ምርጫ የመወዳደሪያ ምህዳሩ ከቀደምት የምርጫ ዘመናት የተለየና የተሻሻለ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው ለክልል ተወዳዳሪዎች አምብዛም ሽፋን ያልሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ግን አማራጭ ሐሳቦቻቸውን በተለያዩ የመንግስትና የግል ሚዲያ አውታሮች እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው ከሰባት በላይ መድረኮችን በመጠቀም የመወዳደሪያ ሐሳቡን ማቅረቡን ገልጸው፤ በዚህም የመወዳደሪያ ምህዳሩ የሰፋ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህ ወቅት በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች በነፃነት ቅሰቀሳ በማድረግና በማሰተዋወቅ ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።
የአፋር ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምርጫውን ሂደት በመገምገም አስፈላጊ የሆኑ የእርማት እርምጃዎችን የሚጠቁም ኮሚቴ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ይህን ኮሚቴ ያዋቀረው ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ያለውን ድርሻ ለመወጣት እንደሆነም አስታውቀዋል።