የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋሉ።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ባህር ዳር ከተማ ከመቻል ጋር ይጫወታል።
ባህር ዳር ከተማ በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። መቻል በ451 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ23ኛ ሳምንት አዳማ ከተማን 2 ለ 0 ያሸነፈው ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ እና ከወራጅ ቀጠና ስፍራ ለመራቅ ይጫወታል።
ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
በሌላኛው መርሐ ግብር አርባምንጭ ከተማ ከሸገር ከተማ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ የመጨረሻው 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሸገር ከተማ በ44 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት 16 የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ዛሬ ከተሸነፈ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ይረጋገጣል።
በ23ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡናን 4 ለ 1 የረታው ሸገር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከልደታ ክፍለ ከተማ ይጫወታሉ።
ሲዳማ ቡና በ31 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ልደታ ክፍለ ከተማ በ19 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ23ኛ ሳምንት በሸገር ከተማ የተሸነፈው ሲዳማ ቡና ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያላሸነፈው ልደታ ክፍለ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና ከወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ ይጫወታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ60 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ 60 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃ የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ23 ግቦች ቀዳሚ ስትሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በ18 ግቦች ትከተላለች።