የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት አተገባበር በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት አተገባበር በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው
ጅማ ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት አተገባበር በምሳሌነት የሚጠቀስና ተጨባጭ መሆኑ ተመላከተ።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመከተል ላይ ትገኛለች። ስትራቴጂው በዋናነት ዘላቂነት ባለው የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና በፈጠራ የታገዙ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ልምዶችን በማስፋፋት ላይ ያተኩራል።
ለአብነትም የአፈር እና ውሃ ጥበቃን ማጠናከር፣ ድርቅ የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን መጠቀም እና ከበካይ ጋዝ ነፃ የሆኑ የኃይል ምንጮችን ማስፋፋት የስትራቴጂው አካላት ናቸው።
ይህም ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጉዞ ከበካይ ጋዝ ልቀት የጸዳ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የያዘችው ግብ አካል ነው።
ለተግባራዊነቱም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የታዳሽ ኃይል ልማት፣ ዘመናዊና አረንጓዴ ትራንስፖርት እንዲሁም የግብርና እና ተፋሰስ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ በኢትዮጵያ የግሎባል ግሪን ግሮዝ ኢንስቲቲዩት (GGGI) ዳይሬክተር እና በኢትዩጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግር እና ኒውትሪሽን የአየር ንብረት አስተባባሪ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የግሎባል ግሪን ግሮዝ ኢንስቲቲዩት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ሁሉን አቀፍና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጥ ጠንካራ ኢኮኖሚን እንዲገነቡ እገዛ ያደርጋል።
በኢትዮጵያ የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ኦኬቹኩ ዳንኤል ኦግቦናያ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ተቋቁማ ያስመዘገበችው እድገት ቀጠናውን በልማት ለማስተሳሰር ተጨማሪ እቅም እየፈጠረ ነው።
የአረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማቱም የካርቦን ልቀትን በመቀነስ የስራ እድል እንዲስፋፋና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ተደማሪ አቅም በመፍጠሩ ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ በታዳሽ ኃይል ልማት በውሃ፣ በነፋስና ጸሐይ ላይ የሚደረጉት ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችም በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት እንደሚያስችላት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግር እና ኒውትሪሽን የአየር ንብረት አስተባባሪ ከፈለኝ ጌታሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረገ እድገትን መገንባት እንደሚያስችላት ጠቁመዋል።
ለዚህም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች ተከላና የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች ምርታማነት እንዲጨምር ማገዛቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የሰሃራ በረሀ መስፋፋትን ተከትሎ በአፍሪካ ቀንድ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተደቀነውን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አየገነባች መሆኗን አስተባባሪው ገልጸዋል።
አትዮጵያ ቀጣናውን በጋራ ልማት ለማስተሳሰር የጀመረችው ተግባርም የሚበረታታ መሆኑንም አክለዋል።