ቀጥታ፡

አገልግሎቱ ከአላስፈላጊ የገንዘብ ወጪ እና እንግልት ታድጎናል - ተገልጋዮች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ከአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት ታድጎናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች ገለጹ፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት ተንቀሳቃሽ አገልግሎትን በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎችና ወደ ንግድ ተቋማት በመንቀሳቀስ ለዜጎች ቀልጣፋና እንግልት የሌለው አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። 

ኢዜአ አገልግሎቱ በሚሰጥባቸው የከተማዋ ስፍራዎች በመዘዋወር ያነጋገራቸው ተገልጋዮች፤ አሠራሩ ከአላስፈላጊ የገንዘብ ወጪና እንግልት እንደታደጋቸው ገልጸዋል፡፡

ከተገልጋዮች መካከል መንጃ ፈቃድ ሲያሳድስ ያገኘነው ወጣት ታምራት መንግሥቱ፤ አገልግሎቱ ደጃፉ ድረስ በመምጣት ተገቢውን ምላሽ እንደሰጠው ተናግሯል፡፡ ቀደም ሲል መንጃ ፈቃድ ለማሳደስ በርካታ ቀናትን ይፈጅ እንደነበር አስታውሶ፣ አሁን በፍጥነትና በጥራት ማግኘት መቻሉን ገልጿል። 


 

ይህም ጊዜና ገንዘብ ሳይባክን፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሳይገታ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻለው አስረድቷል።

ሌላኛው መንጃ ፈቃድ ለማሳደስ የመጡት አቶ ክፍሌ ዳባ በበኩላቸው፤ "አገልግሎቱ ጊዜ ቆጣቢና እንግልትን ያስቀረ ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ብለዋል። 


 

መስተንግዶው እጅግ ትሕትና የተሞላበት፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና እንከን የማይወጣለት መሆኑንም መስክረዋል፡፡

የልደት ምስክር ወረቀት ሲያወጣ ያገኘነው ወጣት መኮንን ይማም በበኩሉ፤ ከአገልግሎት አሰጣጡ ፍጥነትና ጥራት ባሻገር፣ ሠራተኞቹ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነጹ መሆናቸውን በአካል መታዘቡን ገልጿል።


 

"የመንግሥት አገልግሎት በዚህ ልክ ይዘምናል፣ ወደ ደጃፍም ይቀርባል ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም" ያሉት ደግሞ የንግድ ፈቃድ ለማደስ የተገኙት አካል ጉዳተኛው አቶ መኮንን ወርቁ ናቸው። 


 

የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ትልቅ በረከት መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌላኛው መታወቂያ ሲያሳድስ ያገኘነው ወጣት ሚኪያስ ወንድማገኝ፤ አዲስ መሶብ ቢሮክራሲንና የተገልጋዮችን እንግልት ሙሉ በሙሉ ያስቀረ መሆኑን ገልጿል።


 

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ማስረሻ፤ በመዲናዋ እስካሁን የ25 ተቋማት 150 አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ከእነዚህ በተጨማሪ ባለጉዳይ የሚበዛባቸው የስምንት የተለያዩ ተቋማት አገልግሎቶችን በተንቀሳቃሽ መልክ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።


 

ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎቱ ዜጎች ጊዜና ገንዘባቸውን ሳያባክኑ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን እያከናወኑ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንና በደንበኞች ግብረ-መልስ መሠረት የእርካታ ደረጃቸው እያደገ መምጣቱን አረጋግጠዋል። 

ይህም ቀደም ሲል በመንግሥት ተቋማት ይስተዋል የነበረውን የአገልግሎት ስብራት ሙሉ በሙሉ ያስቀረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የአገልግሎቱን አድማስ ለማስፋት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም