ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር (UCI City Mountain Bike Eliminator) ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ይደረጋል።
የዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት (UCI) ዕውቅና የሰጠውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈው "ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ" በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ፣ በኢትዮጵያ የሚካሄድ ይሆናል።
ውድድሩ የሚካሄደው በፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ ነው።
በዓለም አቀፉ ውድድር ላይ ከ24 የአውሮፓ እና ከ10 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ብስክሌተኞች እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውድድሩ ላይ ተሳታፊ ናቸው።
ይህም ኢትዮጵያን በዓመታዊው የዓለም አቀፍ የከተማ ማውንቴንባይክ ካሌንደር ውስጥ ከባርሴሎና በመቀጠል ሁለተኛዋ መዳረሻ ያደርጋታል።
የኤሊት ተወዳዳሪዎች (ወንድና ሴት) የጊዜ ሙከራ፣ የግማሽ ፍጻሜ እና የፍጻሜ ውድድሮች ይከናወናሉ።
ውድድሩ በዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ሲሆን፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ይከታተሉታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዋናው ውድድር አስቀድሞ ትናንት ለሁሉም ክፍት የሆነ ውድድር የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች የመሳተፍ እድል አግኝተዋል።
በዕለቱ የአማተር ብስክሌተኞች፣ የልጆች እና የሰዓት ሙከራ ውድድሮች ተደርገዋል።
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ባወጣው መረጃ ዓለም አቀፍ ውድድሩን ለኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጿል።
ውድድሩ ኢትዮጵያን ለዓለም ከማስተዋወቁ ባሻገር፣ ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ውድድሮች የማዘጋጀት አቅም እንዳላት በተግባር እንደሚያሳይ አመልክቷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች በሀገራቸው ከዓለም ኮከቦች ጋር የመወዳደር እድል እንዲያገኙና ወደ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ እንዲሸጋገሩ ትልቅ ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል ነው ፌዴሬሽኑ ያስታወቀው።
ለኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎም ይታመናል።
በአዲስ አበባ የስፖርት መሰረተ ልማቶች መስፋፋት ከተማዋ ዓለምአቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ ተመራጭ አድርጓታል።
በቅርቡ የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን ውድድር በመዲናዋ መካሄዱ የሚታወስ ነው።