ቀጥታ፡

የእንግሊዝ እግር ኳስ ኃያላን ፍልሚያ፤ ማንችስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ35ኛው ሳምንት መርሐ-ግብር፤ በታሪካዊ ባላንጣነታቸው የሚታወቁት ማንችስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ ተጠባቂ ሆኗል። 

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ይካሄዳል።

ማንችስተር ዩናይትድ በ61 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ሊቨርፑል በ58 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ሁለቱ ክለቦች እስከ አሁን በሁሉም ውድድሮች 244 ጊዜ ተገናኝተው ማንችስተር ዩናይትድ 92  ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ሊቨርፑል 82 ጊዜ አሸንፏል።  70 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ሁለቱ ክለቦች በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባደረጓቸው 67 ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 30 ጊዜ ሲያሸንፍ ሊቨርፑል 20 ጊዜ አሸንፎ 17 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። 

ለ131 ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊ ተቀናቃኝነት ያላቸው ሁለቱ ክለቦች በተመሳሳይ የሊጉን ዋንጫ 20 ጊዜ በማንሳት ስኬታማ ክለቦች ናቸው።

ማንችስተር ዩናይትድ በጊዜያዊ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ እየተመራ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ ይገኛል። 

ዩናይትድ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ያረጋግጣል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመግባት በሚያደርገው ፉክክር የዛሬው ጨዋታ ወሳኝ ነው። 

የ40 ዓመቱ ዳረን ኢንግላንድ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል። 

በሌላኛው የሊጉ መርሐ ግብር አስቶንቪላ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ በቪላ ፓርክ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አስቶንቪላ በ58 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ሲይዝ ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ34 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ጨዋታው አስቶን ቪላ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ፣ ቶተንሃም ደግሞ በሊጉ የመቆየት ህልውናውን ለመታደግ በሚያደርጉት ፉክክር ውስጥ ወሳኝ ትርጉም አለው። 

ዌስትሃም ትናንት መሸነፉን ተከትሎ ቶተንሃም ዛሬ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠና ይወጣል። 

ቦርንማውዝ ከክሪስታል ፓላስ ከቀኑ 10 ሰዓት በቫይታላቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባለፉት 14 የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሰው ቦርንማውዝ በ49 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። ክሪስታል ፓላስ በ43 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም