ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አዲስ ኢንዱስትሪያዊ ስብዕና እና የስራ ባህል እየገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አዲስ ኢንዱስትሪያዊ ስብዕና እና የስራ ባህል እየገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ታምርት ከቴክኒካዊ ብቃት ባሻገር፣ አዲስ ኢንዱስትሪያዊ ስብዕና እና የላቀ የሥራ ባህል በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፤ 830 ፋብሪካዎችን ዳግም ወደ ስራ በማስገባት፣ 4 ነጥብ 85 ቢሊየን ዶላር ገቢ ምርትን በመተካት እና 433 ሚሊየን ዶላር ከኤክስፖርት በማስገኘት አስደናቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር ውጤት ማስመዝገቡንም አመልክቷል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ንቅናቄውን ሲጀምር ግቡ ምርትን ማሳደግና የውጭ ምንዛሬን መታደግ ብቻ እንዳልነበረ አገልግሎቱ ገልጿል።
ከኢኮኖሚያዊ ስሌቶች ባሻገር፣ ትልቁና ስትራቴጂካዊው ስኬት የተመዘገበው ኢትዮጵያን የዕውቀትና የክህሎት ምንጭ በሚያደርገው የሰው ሀብት ልማት ላይ መሆኑ ተመላክቷል።
ዛሬ ላይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የፋብሪካዎች ስብስብ መሆኑ ቀርቶ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚገነቡ ብቁ ባለሙያዎችና መሪዎች የሚፈሩበት ታላቅ የተግባር ትምህርት ቤት መሆን ችሏል።
ይህ ሽግግር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነት ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወደ ቴክኖሎጂ ላኪነትና ክህሎት አቅራቢነት ከፍ የሚያደርግ ለነገዋ ኢትዮጵያዊ መሠረት የሚጥል የታሪካችን እጥፋት መሆኑን ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።
በታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በግዙፍ ፋብሪካዎች ውስጥ የታየው ተጨባጭ ለውጥ የመንግሥትን የፖሊሲ ጥንካሬ በተግባር የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ክፍያ በሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ብቻ ይተዳደሩ የነበሩ ውስብስብ የቴክኖሎጂ ሲስተሞች፣ ዘመናዊ የምርት መስመሮችና የሶፍትዌር መሠረተ-ልማቶች ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ወጣት መሐንዲሶችና ቴክኒሻኖች እየተመሩ ይገኛሉ።
ይህ ስኬታማ የዕውቀት ሽግግር፣ መንግሥት ጥራት ያለው ፖሊሲ የመቅረጽ ብቻ ሳይሆን ፖሊሲን በተጨባጭ ወደ ተግባር የመለወጥና የማስፈጸም አቅም እንዳለው ትልቅ ማሳያ መሆኑ በመረጃው ላይ ተብራርቷል።
በዘርፉ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም የተፈጠረላቸውን ምቹ ዐውድ ተጠቅመው ቴክኖሎጂን የመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ የመግራትና የማላመድ ብቃታቸውን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ።
በዚህም ኢትዮጵያ ለዘመናት የነበረባትን የቴክኖሎጂ ጥገኝነት በፈጠራ አቅማቸው እያስቀሩና አዳዲስ የሥራ ባሕልና የታሪክ ምዕራፍ እየጻፉ መሆኑን አገልግሎቱ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከቴክኒካዊ ብቃት ባሻገር፣ አዲስ ኢንዱስትሪያዊ ሰብዕና እና የሥራ ባህል እየገነባ ይገኛል።
በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች ዓለም አቀፍ የጥራት ቁጥጥር ስታንዳርዶችን፣ ጥብቅ የጊዜ አጠቃቀምንና ስልታዊ የአመራር ክህሎትን በመላበስ ላይ ናቸው።
ከታችኛው የሥራ እርከን ተነስተው በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ እስከ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነት ደረጃ የደረሱ ወጣቶች፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው "ምርጥ ምርት" የሰው ሀብቷ መሆኑን እያስመሰከሩ መሆኑ ተጠቁሟል።
መንግሥት የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ትክክለኛ ፍሬ የሚለካው በወጪ ንግድ ስሌቶች ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ የደረጀና በዕውቀት የበለጸገ አምራች ዜጋ መፈጠሩ መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል።
በመሆኑም ይህን የክህሎት አብዮት ይበልጥ በማፋጠንና ዘርፉን የቴክኖሎጂ ምንጭ በማድረግ፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች በቁርጠኝነት እንደሚቀጥሉም ገልጿል።