ቀጥታ፡

በሀረር ከተማ የኮሪደር ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ

ሐረር፤ ሚያዚያ 24/2018 (ኢዜአ)፦ በሀረር ከተማ የምሽት የአምስት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ።

የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሩን  ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ናቸው።
 

በክልሉ ስፖርት ኮሚሽንና ላንድ አፍሪክ በጋራ አዘጋጅነት የተካሄደው የሩጫ ውድድር "ለብልፅግና እሮጣለሁ ድምፄንም እሰጣለሁ" በሚል መሪ ቃል ነው።

በውድድሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከሐረር ከተማና ገጠር አካባቢ የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና አትሌቶች ተሳትፈዋል።

የሩጫው ውድድሩ ዓላማ በከተማው የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለማስተዋወቅና ስራውን ስኬታማ ያደረጉ እጆችን ለማመስገን ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በውድድሩ ማጠቃላያ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የብልጽግና ፓርቲ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ  ተግባራትን አከናውኗል።

በክልሉ ከተማና ገጠር የተጀመሩ የልማት፣ የቅርስ ጥበቃና ሌሎች ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች የሜዳልያና የገንዘብ ሽልማት ከዕለቱ ክብር እንግዳ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪና ከሌሎች እንግዶች እጅ ተበርክቶላቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም