ተፈጥሯዊና የባህል ሀብቶችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ተፈጥሯዊና የባህል ሀብቶችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው
ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ የተፈጥሯዊና የባህል ሀብቶችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተመላከተ።
"በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቱሪዝም ልማት ውስጥ ፈጠራና ዘላቂነት" በሚል መሪ ሀሳብ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 15ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ተካሂዷል።
በኮንፈረንሱ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ የትምህርት መስክ ተማሪዎችን ከማሰልጠን ባለፈ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማድረግ ዘርፉ ለሀገር እድገት ያለውን ፋይዳ ለማሳደግ የበኩሉን እየተወጣ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ በተጀመረው ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትወልድ መርሀ ግብር በርካታ የመስህብ ስፍራዎች መልማታቸውን የማልማት ሥራ መሰራቱን ለማሳያነት ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ተፈጥሯዊና የባህል ሀብቶችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አክለዋል።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ በዓለማችን እጅግ ከፍተኛ ትኩረት እያገኙ ከመጡ የሥራ መስኮች አንዱ ነው።
በአትዮጵያ በርካታ የመስህብ ሥፍራዎች ቢኖሩም አልምቶ ከመጠቀም እንጻር ተግዳሮቶች እንደነበሩ አስታውሰው፣ በለውጡ መንግስት የመዳረሻ ስፍራዎችን በማስፋፋት ኢትዮጵያ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ተሰርቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና በኮንፈረንሱ ጥናት ያቀረቡት ይታሰብ ስዩም፣ በዘመናዊ የቱሪዝም ልማት ውስጥ አዳዲስ ፈጠራና ዘላቂነትን መሰረት ያደረገ የማልማትና ማስተዋወቅ ሥራ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የቱሪዝም መሰረተ ልማትን ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰርና አገልግሎቱን ማዘመን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳውን ከማሳደግ ባለፈ ሀብቱ ለትውልድ እንዲተላለፍ ያግዛል ብለዋል።
በስነምህዳር ቱሪዝም (ኢኮ ቱሪዝም) ዙሪያ የምርምር ሥራቸውን ያቀረቡት በቦረና ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ጸለፎ ጫካ፣ በሀገራችን ቱሪዝምን ከስነምህዳር ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ ያለው ሥራ በርካታ ጎብኚዎችን እየሳበ መሆኑን ገልጸዋል።
የመዳረሻ ልማት ሥራዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ፣ ባህል፣ አኗኗር እና አረንጓዴ አሻራን ያስተሳሰረ በመሆኑ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና በከተሞች የተጀመረውን የቱሪዝም መሰረተ ልማት ተደራሽነት ወደ ሌሎች ማስፋፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ከቱሪዝም ጋር የተያያዙ ጥናታዊ የምርምር ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን ከሀዋሳና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተወከሉ ምሁራን፣ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት መምህራንና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።