ባሳለፍነው ሳምንት … - ኢዜአ አማርኛ
ባሳለፍነው ሳምንት …
ከሚያዝያ 18 እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል …
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን
በአዲስ አበባ በሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኘውን "ጎበዝ ሶላር ሴል" ማምረቻን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት የጎበኙ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅትም ይህ ፋብሪካ በ2025 ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያድርጉ ፎረም (Invest in Ethiopia Forum) አማካኝነት በተፈረመው ስምምነት መነሻ በ100 ሚሊየን ዶላር የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ የተቋቋመ ነው ብለዋል።
በውጤታማ ድጋፍ እና ክትትል በስድስት ወራት ብቻ እውን የሆነው "ጎበዝ ሶላር ሴል" ማምረቻ ዘመናዊ ማሽኖች እና በቴክኖሎጂ የተዋቀረ መሆኑን ገልጸው፣ ማምረቻው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድልም ፈጥሯል ነው ያሉት። በመጀመሪያ ምዕራፍ 2 ጌጋዋት ዓመታዊ የማምረት ዐቅም ያለው ፋብሪካው የኢትዮጵያን የኃይል ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ ኃይል ለማድረግ ለተጀመረው ሀገራዊ ርዕይ እውን ለማድረግ ተደማሪ ዐቅም ፈጥሯል ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የሚገኘውን የጫማ ማምረቻ እና ንዑስ የኤሌክትሪክ ጣቢያን ተመልክቻለው ብለዋል በመልዕክታቸው።
• ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራዳ ፓርክን መመረቃቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት አራዳ ፓርክን በመረቁበት ወቅት፤ ፓርኩ አዲስ አበባን ለመለወጥ ያለንን ርዕይ በተግባር ያሳየንበት አንዱ ሥራችን ነው ብለዋል። ቀደም ሲል ተዘንግቶና ለአደጋ ተጋልጦ የነበረው የአራዳ አካባቢ፤ ዛሬ ተመልሶ ተገንብቶ አስደናቂ የከተማ አካል መሆን ችሏል ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለእኛ በምናብ የምትሳል ህልም ብቻ ሳትሆን በተግባር የምትገነባ እውነታ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጤናማ፣ ጽኑ፣ ለመጭው ትውልድ ተስፋን ከተጨባጭ ሀብት ጋር የምትሰጥ፣ በአፍሪካ መሪ፣ በዓለም መድረክ ደግሞ ተወዳዳሪ የሆነች ሀገር እየገነባን እንገኛለን ብለዋል። በየቀኑም ተስፋን ወደ እውነታ የመለወጥ ተግባራችንን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ መድረክ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተገኝተው ሐሳባቸውን ያጋሩበት “የማኅበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀውና በማኅበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች የቀረቡበት የምክክር መድረክ ባሳለፍነው ሳምንት ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የማኅበራዊ ዘርፍ ግንባታ እንደ ሌሎች መሠረተ-ልማቶች ውጤቱ ወዲያው የሚታይና የሚጨበጥ ባይሆንም፤ ለሀገር ዘላቂና ወሳኝ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በሚገጥሟት ተግዳሮቶች ሳትገደብ ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባች መሆኗን ገልጸው፤ ምንም እንኳ የዐቅም ውስንነቶች ቢኖሩብንም ለማሻሻል ያልተሞከረ የማኅበራዊ ዘርፍ የለም ሲሉም አስረድተዋል።
በየዘርፎች የታለመው ሁሉ በተግባር እንዲተረጎምና ተገቢውን ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም አንድ እጅ ብቻውን ማጨብጨብ እንደማይችል ሁሉ፤ መንግሥት የሚጀምራቸውን ሥራዎች ሌላው የማኅበረሰብ ክፍል እንደ አንድ ባለ ድርሻ ኃላፊነት ወስዶ በጋራ መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
• የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ
ባሳለፍነው ሳምንት የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ዳንኤል ፍራንሲስኮ ቻፖ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በክብር ተቀብለዋቸዋል። የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የጋራ ልማትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ትርጉም ባለው መልኩ ሊለውጡ የሚችሉ ተጨባጭ ሥራዎችን ቅድሚያ የሰጠ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለእውነተኛ አፍሪካዊ አጋርነት ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከዚያም ባደረጉት ቆይታ ዘላቂ እና ተጨባጭ ለውጥ ለሚያመጣ አጋርነት መሠረት የጣለ ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በስትራቴጂካዊ ዘርፎች ያለንን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩና የአሠራር ማዕቀፍ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የመግባቢያ ሠነዶችን ልውውጥ አካሂደናል ብለዋል።
• የበጋ መስኖ እርሻ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የበጋ መስኖ እርሻ በምግብ ራሳችንን ለመቻል በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የጸና መሠረት የጣልንበት ምዕራፍ ነው ብለዋል።
የውኃ ሀብታችንን በአግባቡ በመጠቀም፣ ባልተቋረጠ ጥረት እና ቁርጠኝነት፣ የመልማት ጉዟችን አስተማማኝና ዘላቂ የሆነ የምግብ ዋስትና ወደምናረጋግጥበት ብሩህ ተስፋ እንደሚያሸጋግረን ጥርጥር የለውም ሲሉም አስገንዝበዋል።
• ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባሳለፍነው ሳምንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሆሞሻ ወረዳ የሚገኘውን ፍቃዱ ነመራ የተቀናጀ የእርሻ ልማት ጎብኝተዋል። ጉብኝታቸውን ተከትሎም፤ ፍቃዱ ነመራ የተቀናጀ የእርሻ ልማት በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የግብርና ሥራ እንዲስፋፋ ለሚደረገው ሥራ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል። ይህ በግል ባለሀብት እየለማ ያለው የግብርና ሥራ እንደ ሶላር ያሉ የኃይል አማራጮችን እና የከርሰ ምድር ውኃን በመጠቀም በመስኖ በማልማት ኢትዮጵያ ለጀመረችው የግብርና ልማት እና የገጠር ሽግግር ሰፊ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግራናይት የሚያመርተውን የኦርላመንት (3ኤም) ማርብልና ቴራዞ ማኑፋክቸሪንግ የሥራ እንቅስቃሴ የጎበኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት የግሉ ዘርፍ በማዕድን ልማት ላይ በስፋት እንዲሳተፍ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ፣ ማበረታቻና ድጋፍ እንዲህ ያሉ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ ነው ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከወርቅ እስከ ግራናይት በተፈጥሮ የታደለ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ፀጋ ለሀገር ብልጽግና ለማዋል የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።