ቀጥታ፡

በክልሉ የጤና ተቋማትን ተደራሽነት የማረጋገጥ ቅንጅታዊ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሚዛን አማን፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የጤና ተቋማትን ተደራሽነት የማረጋገጥ ቅንጅታዊ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ ፍቅሬ አማን ገለጹ።

በክልሉ ሚዛን አማን ከተማ በግሉ ባለሀበት ከ250 ሚሊዮን በሚበልጥ ብር የተገነባው "ኒቆ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል" ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

አቶ ፍቅሬ አማን ሆስፒታሉን መርቀው ሲከፍቱ እንዳሉት የጤና ዘርፍ ኢንቨስትመንት ሕይወት የመታደግ ተግባር በመሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።

 

የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማሳካት ለመንግስት ብቻ የሚተው አለመሆኑንና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

የጤና ተቋማትን ተደራሽነት ለማሳደግ የግሉን ዘርፍ አጋርነት የማጠናከር ሥራ ላይ  ትኩረት መደረጉን ገልጸው፣ ዛሬ የተመረቀው የኒቆ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የዚሁ አካል  ነው ብለዋል።

  

በመደመር መንግሥት እሳቤ የግሉን ዘርፍ እና የሕዝብ ተሳትፎ ከመንግሥት ተግባር ጋር በማቀናጀት የሚሰሩ ልማቶች ውጤታማ በመሆናቸው ጎልብተው እንዲቀጥሉ ይሰራል ነው ያሉት።

 

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው በዞኑ የጤና ተቋማትን ተደራሽነት ማስፋፋትና ግብዓት የማሟላት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል።

  

በተለይ የግሉ ባለሀብት በጤናው ዘርፍ እያደረገው ያለው ተሳትፎ በመንግስት የጤና ተቋማት የሚፈጠርን የአገልግሎት ጫና እንደሚያቃልል አንስተዋል።

 

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰሎሞን ሌዊ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በከተማዋ ሦስት የግል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

 

ይህም መንግስት ለዘርፉ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ያሳያል ያሉት ከንቲባው፣ ሕዝቡ ጤናው ተጠብቆ ልማትን እንዲያፋጥን ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ ኢንቨስትመንት የሚያደርገውን እገዛ ይቀጥላል ብለዋል።

 

የሆስፒታሉ ባለቤት ኒቆዲሞስ ዓለሙ ለሆስፒታሉ ግንባታ ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውንና ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ሆስፒታሉን በዘመናዊ የሕክምና ቁሳቁስ ማደራጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም