ቀጥታ፡

በዞኑ በመኸር እርሻ በዘር ከሚሸፈነው መሬት ከግማሽ በላይ የሚሆነው በኩታ ገጠም የሚለማ ነው

ደሴ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ወሎ ዞን በመጪው የመኸር እርሻ በዘር ከሚሸፈነው 432 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በኩታ ገጠም እንደሚለማ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

አስተዳደሩ የ2018/19 መኸር ምርት ዘመን የሰብል ልማት ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በደሴ ከተማ አካሂዷል።


 

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አሊ ይማም በመድረኩ እንደገለጹት፣ የመኸር እርሻ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት የተያዘውን ግብ የሚሳካበት ነው።

በመኸር እርሻ ከሚለማው 432 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ249 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በኩታገጠም እንደሚለማ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ለመሰብሰብ ከታቀደው ከ16 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ከ10 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የሚሆነው በኩታ ገጠም ከሚለማው ሰብል እንደሚሰበሰብ አስታውቀዋል።

በልማቱ ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራሮችን እንዲሁም ግብዓትን በአግባቡ መጠቀም ላይ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው በመኸሩ የታቀደውን ምርት ለማግኘት ለአርሶ አደሩ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

በተለይም የሜካናይዜሽን እርሻ ላይ በማተኮርና የተሻሻሉ የግብርና አሰራርና ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር የምርት ዕድገትን ለማረጋገጥ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም