በክልሉ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ልማትን ለማስቀጠል ያላቸውን እቅም እንዲያጠናክሩ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ልማትን ለማስቀጠል ያላቸውን እቅም እንዲያጠናክሩ እየተሰራ ነው
ባህርዳር፤ ሚያዚያ 24/2018 (ኢዜአ)፦ የልማት ድርጅቶች በክልሉ እድገት ውስጥ ያላቸውን አበርክቶ እንዲያጠናክሩ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ገለጹ።
በአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የተቋቋመው አልማኮን የህንጻ ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ማምሻውን አዲስ ብራንዱ ይፋ ተደርጓል።
የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ለማሳደግ የአጋር አካላት ተሳትፎ የጎላ ሚና እያበረከተ ነው።
በመሰረተ ልማት ግንባታና ማህበራዊ ልማት ላይ በመሳተፍም የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አጋር አካላቱ እገዛ እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዚሁ ማሳያ የሆነው አልማኮን በአዲስ ብራንድ መምጣቱ የተሰጠውን ተልእኮ በብቃት በመፈጸም የክልሉን እድገት ለማፋጠንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ ይብልጥ እንዲያጠናክር ያደርገዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልል የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በክልሉ እድገት ውስጥ ያላቸውን አበርክቶ እንዲያጠናክሩም ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት።
የአማራ ልማት ማህበር /አልማ/ ዋና ስራ አስፈጻሚና የአልማኮን ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ በበኩላቸው ፤ ማህበሩ ሀብት የሚያመነጩ ተቋማትን በማቋቋም ከእርዳታ ጠባቂነት ለመውጣት እየሰራ ይገኛል።
አልማኮን የተሰኝው ተቋምም በኮንስትራክሽን፣ በሪል እስቴት ልማትና በግንባታ ግብዓት አቅርቦት ላይ እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት።
ኩባንያው በአዲስ ብራንድ መምጣቱም በኮንስታራክሽንና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተወዳዳሪ ምርቶችን ይዞ ወደ ገበያ በመግባት የክልሉን እድገት ለፋጠን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንደሚያስችለው አስረድተዋል።
የአልማኮን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰጥቷል ደሳለኝ እንደገለጹት፤ ኩባንያው በ2005 ጀምሮ በኮንስትራክሽን ዘርፉ በመሰማራት ለክልሉ እድገትና ለህዝቡ ተጠቃሚነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ኩባንያው አዲስ ብራንድ ይዞ መምጣቱም በአምስት ዓመት ስትራቴጅክ እቅዱ መሰረት አዲስ አደረጃጀትና አሰራር በመፍጠር የገበያ አድማሱን ለማስፋት እንደሚያስችለው አስገንዝበዋል።
በመደረኩ ላይም በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረሥ ሳህሉ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ የቢሮ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።