የመምህራንን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት የክልሉ መንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የመምህራንን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት የክልሉ መንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያደርጋል
ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ የመምህራንን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት የክልሉ መንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ፡፡
አቶ ደስታ ሌዳሞ የክልሉ መምህራን ማህበር ለሚያስገነባቸው የመምህራን ሆስፒታል እና ሁለገብ ሕንጻዎች ግንባታ ሥራ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት መምህራን በክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑንና በተለይ ከማህበሩ ጋር በመቀራረብ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የትምህርት ሥብራትን ለመጠገንና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ለግንባታ ሥራው ማስጀመሪያ የሚሆን 50 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉንና ሕንፃው ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ የክልሉ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው መምህራን በትውልድ ግንባታ ውስጥ ተሳትፏቸው ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የመምህራን ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲሻሻል፣ ምቹ የሥራ አካባቢ እንዲኖራቸውና ጤናቸው በአግባቡ ተጠብቆ በበለጠ ትጋት እንዲሰሩ ለማስቻል ማህበሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፕሮጀክት ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ኢያሱ ፍቅሬ የክልሉ መምህራን ጠንካራ የትምህርት ሥርዓትን ለመገንባትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ማህበሩ ከ46 ሺህ በላይ አባላትን በሥሩ መያዙን ጠቁመው የመምህራን መታከሚያ ሆስፒታልና ሁለገብ ሕንጻዎቹ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በክልሉ በየደረጃው በመንግስት እየተደረገላቸው ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስግነው የማህበሩ አባላት ትውልድ የመቅረጽ ሀላፊነታቸውን በበለጠ ተናሳሽነትና ትጋት አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ለመምህራን ሆስፒታል የሚገነባው ሕንጻ ባለ 6 ወለል መሆኑን ገልጸው፣ ሁለገብ ሕንጻው ባለ 12 ፎቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕንጻዎቹ በ1ሺህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፉ ገልጸው ለግንባታቸውም በአጠቃላይ ከ900 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።