ቀጥታ፡

አገልግሎት ለዜጎች፣ ክብር ለሕዝብ

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ውስጥ የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ ቁልፍ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል። መንግስት የአገልጋይነት መርህን መሰረት በማድረግ፣ በአስተዳደራዊ መዋቅሮችና በማህበረሰቡ መካከል ጠንካራ ድልድይ ለመገንባት የተለያዩ የሪፎርም እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ። ከዚህ አንፃር ማንኛውም የመንግስት አመራር እና ሰራተኛ  በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል አለበት ፡፡

የመደመር መንግስት እንደሚለው፣ የአንድ አስተዳደር መኖር ትርጉም የሚሰጠው ዜጎች በሚፈልጉት ቦታና ሰዓት ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊና ከሌብነት የጸዳ አገልግሎት ማግኘት ሲችሉ ብቻ ነው። አገልግሎት አሰጣጥ እንደ ተራ የመንግስት ግዴታ ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝብና በመንግስት መካከል ያለውን መተማመን የሚገነባ ዋነኛ መሣሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ለዚህም ሲባል መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ውሃና ፍትህ ያሉ ዘርፎች የዜጎች ሰብዓዊና ዜግነታዊ መብት እንጂ ከመንግስት የሚሰጡ ችሮታዎች አይደሉም ። በዚህም መሰረት የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ፣ በሙያዊ ብቃትና በገለልተኝነት ዜጎችን እኩል የሚያስተናግዱበትን ስርአት መገንባት ለሀገረ-መንግስቱ ፅናት ወሳኝ መሆኑ ይታመናል ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ መንግስት ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ሰፋፊ የህግና የመዋቅር ማሻሻያዎችን አድርጓል። ከእነዚህም መካከል በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ እንደ አንዱ አብይ ምሶሶ ተቀርጾ እየተተገበረ ይገኛል። ዜጎች ለአንድ አገልግሎት ብዙ መስሪያ ቤት በመመላለስ እንዳይጉላሉ "መሶብ" የተሰኘ ዘመናዊ የአንድ ማዕከል አገልግሎት  በማስጀመር የሌብነት ዕድልን መቀነስ ተችሏል። በተጨማሪም "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ አማካኝነት የንግድ ፍቃድ፣ የፓስፖርት አገልግሎትና የታክስ ክፍያ መሰል አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል ተቀይረዋል። ይህም ለዜጎች ከፍተኛ የጊዜና የጉልበት ብክነትን ከማስቀረቱም  በላይ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት በስራ ሂደት ውስጥ እንዲሰፍን አድርጓል።

በተለይም በፍትህ ዘርፍ የዳኝነት ነፃነትን ለማረጋገጥና ተቋማቱን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ ነው። በጤናው ዘርፍ የጤና መድህን ስርአት በመስፋፋቱ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል። በትምህርት ዘርፍም የብሄራዊ ፈተና አሰጣጥ ስርአት በማሻሻልና የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን በመተግበር የትውልድ ግንባታ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። እነዚህ ውጤቶች በዜጎች ዘንድ የመንግስት ተቋማት ቅቡልነት እንዲጨምርና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ስሜት እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

ወደፊትም መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማዘመን ታላላቅ እቅዶችን ነድፏል። የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን  በሀገር አቀፍ ደረጃ በማስፋፋት ቢያንስ 80 በመቶ የሚሆኑ የመንግስት አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሰጡ የማድረግ ግብ ተቀምጧል። ይህ "ሙሉ ዲጂታላይዜሽን" እቅድ የተወሳሰበ ቢሮክራሲንና ሙስናን ለዘላቂው ለመቅረፍ እንደ ዋና መፍትሄ ታይቷል። በተጨማሪም በብቃት ላይ የተመሰረተ የሲቪል ሰርቪስ ስርአት በመገንባት፣ የዜጎችን ግብረ-መልስ በቀጥታ የሚቀበል የክትትል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዷል። ይህም ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው ተቋማትና አመራሮች ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርአት ይፈጥራል። በአጠቃላይ መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ስብራትን በመጠገን፣ ዜጎች በሀገራቸው ተከብረውና ተደስተው የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ፡፡

ብልፅግና ፓርቲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም