ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ  ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትንና ፌዴራላዊ ሥርዓትን የማፅናት አዲስ አቅጣጫ

ከለውጡ በፊት ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በተሟላ ሁኔታ አለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መዋቅሮች ላይ ጥልቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል ፡፡ ቀደምት ግጭቶች፣ የመሠረተ ልማት ውድመትና የማኅበራዊ ትስስር መላላት የዚሁ አንድነት አለመረጋገጥ ውጤቶች ናቸው ፡፡ የመደመር መንግስት  እየገነባ ያለው  ሥርዓት ልዩነቶችን እንደ ጌጥ፣ አንድነትን ደግሞ እንደ መሠረት የሚቀበል "ባለ ሚዛን" ሥርዓት ነው ይህ አዲስ ጉዞ የቡድን መብትንና የግለሰብ ነፃነትን ሳያጋጭ በማጣጣም፣ የሀገረ መንግሥቱን ፅናት ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

ይህ ዕሳቤ ኅብረ-ብሔራዊነትን እንደ ነባር ሀገራዊ እውነታ የሚቀበል እንጂ ከአንድነት ጋር የሚጋጭ አድርጎ አይመለከተውም። በዚህም መሠረት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰቡ የሚገነባው በወል ትርክትና ለብዝኃነት እውቅና በሚሰጡ እሴቶች ላይ ይሆናል። መንግሥት "በኅብረት ሆነን እንበለጽጋለን" በሚል መርሕ፣ በቀጣይ ዓመታት የብዝኃ ቋንቋ ፖሊሲን ወደ ተግባር በማስገባትና የፌዴራል ሥርዓቱን ዋና ምሶሶ የሆነውን ብዝኃነትን በማስተናገድ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል

ባለፉት የለውጥ አመታት ከተከናወኑት መካከል  ቀደም ሲል "አጋር" ተብለው ከውሳኔ ሰጪነት ተገልለው የነበሩ የዳር አካባቢ ሕዝቦችን እንደ ሀገር ግንባታ ዋና ምሰሶ በማየት ማካተቱ ትልቅ እርምጃ ነው ፡፡ በተጨማሪም፣ በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት በሕግ ለመምራት የወጣው አዋጅ (1231/2013) እና ለዘመናት ታፍነው የነበሩ የማንነት ጥያቄዎች በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ምላሽ ማግኘታቸው እንደ ስኬት ይጠቀሳሉ እነዚህ እርምጃዎች በዜጎች መካከል የመተማመን መንፈስ እንዲጎለብትና ክልሎች እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉበት "እህትማማችነት" ፖለቲካ እንዲሰፍን አድርገዋል ፡፡

ኢኮኖሚያዊ ፋይዳን በተመለከተ፣ መንግሥት የፌዴራል ሥርዓቱን የክልሎችን ጸጋ ለጋራ ብልጽግና ማዋያ መሣሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ይገኛል። ለዚህም እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የሕዝብ ትስስር ምልክቶች፣ "ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክቶች እና በቆላማ አካባቢዎች የተመዘገበው የስንዴ ልማት ተሞክሮዎች በዋቢነት ቀርበዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ክልሎች ያላቸውን አቅም ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከመቀየር ባለፈ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ብሔራዊ አንድነትን አፅንተዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች የሚከናወኑ የኮሪደር ልማቶችና የታሪክ መዘክሮች ግንባታም የኢትዮጵያን ብዝኃነትና የጋራ ማንነት የሚያንፀባርቁ ናቸው።

መንግሥት ተቋማዊ ሪፎርሞችን በማጠናከር ሲቪል ሰርቪሱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግ እሰራ ይገኛል የብዝኃ-ልሳን ፖሊሲን ማስፋፋት፣ የክልሎችን የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከርና በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በኩል የሚመጡ የመፍትሔ ሀሳቦችን  ተግባራዊ ማድረግ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው። በተጨማሪም፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ቀመርን በማሻሻል አነስተኛ አቅም ያላቸውን አካባቢዎች የሚደግፍ አሠራር ይዘረጋል የመደመር  መንግሥት የሚከተለው የፌዴራሊዝም አቅጣጫ ኢትዮጵያን ጠንካራ ተቋማት ያሏት፣ ብዝኃነቷ ለልማት የሚውልባትና እያንዳንዱ ዜጋ በነፃነት የሚኖርባት ሀገር ለማድረግ ያለመ ነው

ብልፅግና ፓርቲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም