ቀጥታ፡

አርሶ አደሮች ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ መቅረቡ ለግብርና ሥራቸው ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ተናገሩ

ወልቂጤ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- ለበልግ ወቅት አዝመራ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ ማግኘታቸው ለግብርና ሥራቸው ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉራጌ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።


 

የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ወቅቱን ጠብቆ መቅረቡ ለግብርና ልማት ሥራቸው መሳካት ከፍተኛ ዐቅም መፍጠሩን የአበሽጌ ወረዳ አርሶ አደር ሰብስቤ ወልደሃዋርያት ተናግረዋል።

ከአራት ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ እስካሁንም ሦስት ሄክታር መሬታቸውን በበቆሎ እና በማሽላ ምርጥ ዘር መሸፈናቸውን አስረድተዋል።


 

አርሶ አደር ፍቃደ ተበቃም የቀረበላቸውን የአፈር ማዳበሪያ ተጠቅመው ማሳቸውን በበቆሎ ዘር እንደሸፈኑ ገልጸዋል።


 

በዞኑ ከ82 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ አዝመራ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አበራ ወንድሙ ናቸው።

በበልግ እርሻ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ድንችና ሌሎች ሰብሎች እንደሚለሙ ጠቅሰው፤ እስካሁን 34 ሺህ ሄክታር ማሳ በድንች ዘር መሸፈኑን አረጋግጠዋል።

በ46 ሺህ ሄክታር ላይ በቆሎ እንደሚለማ ጠቁመው፤ በግንባር ቀደም አርሶ አደሮችም በሄክታር ከ121 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ግብ ተጥሏል ብለዋል።

የበልግ አዝመራ ልማቱን ለማሳካት 8 ሺህ 200 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ቀመቅረቡን ጠቁመዋል።

ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ተዘጋጅቶ ለግብርና ሥራው ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም