ኢንተርፕራይዞቹ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዞቹ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው
ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በመንግሥት የተደረገላቸው ድጋፍ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዳስቻላቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያየ የሥራ መስክ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ገለፁ፡፡
በጉራጌ ዞን አረቅጥ ከተማ የወሄነት ዳቦ ማምረቻና መሸጫ ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ ወጣት መሰረት ወልዴ እንዳለችው፤ ኢንተርፕራይዛቸው ከአባላቱ አልፎ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
ከሦስት ዓመት በፊት በመንግሥት በተመቻቸላችው የ50 ሺህ ብር ብድር የማምረቻና የመሸጫ ሼድን ጨምሮ በተሰጣቸው የሥልጠና ድጋፍ ወደ ሥራ መግባታቸውን አውስታለች።
ማኅበሩ አሁን ላይ የአባላቱን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አልፎ፤ ለ 25 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን እና ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገቡን ለኢዜአ አረጋግጣለች።
በቡታጅራ ከተማ የሚገኘው የአድማሱ ቶርኖ ሥራዎች አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ ወጣት ዳዊት አድማሱ፤ ኢንተርፕራይዙ የአርሶ አደሩን ምርት አሰባሰብ ሂደት የሚያዘምኑ ማሽኖችን መሥራቱን ገልጿል።
ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ከመጠቀማቸው አልፎ፤ ለ13 ወጣቶችም የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግሯል።
ኢንተርፕራይዙ በ300 ሺህ ብር ሠራ መጀመሩን አውስቶ፤ አሁን ላይ ካፒታሉ 5 ሚሊየን ብር ደርሷል ብሏል።
የውኃ መሳቢያ ፓምፕ እና ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችን ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ በሆሳዕና ከተማ የሚገኘው የአሚቼ ብረታ ብረትና እንጨት ሥራዎች ቴክኖሎጂ ሽግግር አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ ተካልኝ ዓለሙ ነው።
በተሰማሩበት ዘርፍ ተጠቃሚነታቸው እያደገ ከመምጣቱ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ሌሎች ወጣቶችን እያሰለጠኑ መሆኑንም አስታውቋል።
በክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሙስጠፋ ኢሳ እንዳሉት፤ በአነስተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ ለሚገኙ 3 ሺህ 620 አምራች ኢንተርፕራይዞች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው።
ኢንተርፕራይዞቹ ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል።