በከተማዋ የተገነባው የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሕንፃ ምቹ የሥራ ሁኔታ ለመፍጠርና ገቢን ለማጠናከር ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የተገነባው የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሕንፃ ምቹ የሥራ ሁኔታ ለመፍጠርና ገቢን ለማጠናከር ያስችላል
ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ በባህር ዳር ከተማ የተገነባው የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሕንፃ ምቹ የሥራ ሁኔታን ለመፍጠርና ተጨማሪ ገቢን ለማጠናከር እንደሚያስችል የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።
በመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በባህር ዳር ከተማ የተገነባው ባለ 9 ወለል ዘመናዊ መንትያ ሕንፃ ወደ ሥራ ገብቷል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በምረቃው እንደገለጹት ከጣና ሐይቅ በቅርብ ርቀት ላይ የተገነባው ሕንጻ በአካባቢው ከለማው የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራ ጋር ተዳምሮ የከተማዋን ገጽታ የቀየረ ነው።
መንትያ ሕንፃው ከቢሮ አገልግሎት በተጨማሪ ለመዝናኛ፣ ለንግድ እንቅስቃሴ፣ ለስብሰባና ለቱሪዝም አገልግሎት የሚውል መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም ለተቋሙ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን ኢኮኖሚያዊ አቅምን ከማጠናከር ባለፈ ምቹ የሥራ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አስቻለው ሞላ በበኩላቸው መንትያ ሕንጻው ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ የተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በጠቅላላ 2ሺህ 640 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ሕንጻ ከቤዝመንት በተጨማሪ ዘጠኝ ወለል እንዳለውና ግንባታውም በተያዘለት ጊዜ እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል።
ሕንጻው ለተለያዩ አግልግሎቶች የሚውል በርካታ ክፍሎች ያሉትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት መሆኑንም አመልክተዋል።
የሕንጻው ግንባታ ተቋሙ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም አክለዋል።