የምንፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ግንቦት 24ን እየጠበቅን ነው - የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምንፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ግንቦት 24ን እየጠበቅን ነው - የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች
ጂንካ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በተመቻቸልን ዕድል ተጠቅመን የምንፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለንን የምርጫ ካርድ በመውሰዳችን ግንቦት 24ን በጉጉት እየጠበቅን ነው ሲሉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለፁ።
ተማሪ በቀለ ባሪሶ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ ምርጫው የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ በንቃት ተሳትፎ ለማድረግ መቻል ልዩ ስሜት አለው።
ምርጫው የዴሞክራሲ ልምምድ ሥርዓት አካል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ መሳተፍ አለበት ያለው ደግሞ ተማሪ አምሳሉ ዓባይነህ ነው።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያበቃውን የድምፅ መስጫ ካርድ በመውሰዱ ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምጹን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም አንስቷል።
የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት መቅደስ አድማሱ በበኩሏ አብዛኛው ተማሪ በምርጫው ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ይህም ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን አስረድታለች።
ዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽ ኮሙኒኬሽን እና የቤተ ሙከራ ማዕከላትን በበይነ መረብ በማስተሳሰር ተማሪዎች ዲጂታል የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ማድረጉን የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት መልካሙ ዘሮ (ዶ/ር ) ተናግረዋል።