ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ የንግድ ስርዓቱን ከማዘመን ባለፈ በማህበራዊ ኃላፊነት ዘርፍ በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው

ሮቤ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ የንግድ ስርዓቱን ከማዘመን ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመቀናጀት በባሌ ሮቤ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ያስገነባቸው መኖሪያ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች አስረክቧል።

የተገነቡት 20 መኖሪያ ቤቶች እያንዳንዳቸው የራሳቸው መሰረተ ልማትና የመኖሪያ ቁሶቁሶችን የተሟላላቸው መሆኑም ነው የተገለፀው።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ተቋሙ የንግድ ስርዓቱን ከማዘመን ባለፈ የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ከዚህ ውስጥም በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይ ዜጋ ተኮር ልማቶችና አገልግሎቶችን በማካሔድ ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

ዛሬ በባሌ ሮቤ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት እነዚሁ ፕሮጀክቶች የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቶቹ በተለይ የአቅመ ደካማ ወገኖች የመኖሪያ ቤት ችግርን የሚቀርፉ ከመሆናቸው ባሻገር ፤ በዘርፉ የተያዙ ሀገራዊ ግቦችን ከማሳካት መንፃር ጉልህ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያካሒደውን የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ይበልጥ የሚያጠናክሩና ቀጣይነት ያላቸው መሆናቸውንም አንስተዋል።

ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት በራሳቸውና ሌሎች አካላትን በማስተባበር የገነቡትን ዲጂታል መፀሐፍት ቤት ለቀድሞ ትምህርት ቤታቸው የሮቤ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስረክበዋል።

የመጽሃፍት ቤት ግንባታው የከተማዋን ወጣቶችና ተማሪዎች የንባብ ባህል ይበልጥ የሚያሳድግ ሲሆን የልጅነት ሕልማቸውንም ለማሳካት ያስቻላቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዲኖ አሚን በበኩላቸው ፤ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለከተማዋ እድገትና ለአቅመ ደካማ ዜጎች ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከተማዋን ለነዋሪው ምቹና የንግድ ማእከል ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እገዛ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የገለጹት።

ከልማቱ ተጠቃሚዎች መካከል ሼህ አልይ ከድርና ወይዘሮ ፋጡማ አብዳላ በበኩላቸው፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታው ለዓመታት የነበረባቸውን የመጠለያ ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም