ቀጥታ፡

በአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትል ለማረጋገጥ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና የላቀ ነው

ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትል ለማረጋገጥ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ።

’’አርብቶ አደሮችና ትምህርት’’ በሚል መሪ ሃሳብ 2ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ዛሬ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በኮንፍረንሱ እንደገለጹት፣ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማስፋፋት በሰራቸው ተግባራት ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በቀጣይም የተጀመሩ ኢንሼቲቮችና ስኬቶችን ይበልጥ በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ልማት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በማህበራዊ ልማት በተለይም የአርብቶ አደሩን የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህ ረገድ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል ከማፍራት ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማውጣት   ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውሉ ሲያከናውኑ የቆዩትን ስራዎች ማጎልበት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም በአርብቶ አደሮች አካባቢ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ለልማት እንዲውል በምርምር በማገዝ የአርብቶ አደሩ ሕይወት እንዲለወጥ በማድረግ በኩል የላቀ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

በተለይም የአርብቶ አደሩን የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ለማሳደግ የሚያግዙ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።


 

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ጎን ለጎን በአካባቢያቸው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት የሚቀየርበትን አቅም በምርምር  እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

ዛሬ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስም በቀጣይ ለሚወጡ ሀገራዊ የልማት ፖሊሲዎች ጠቃሚ ግብዓቶች ለማፍለቅ ያግዛል ብለዋል።


 

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ድሪባ ኢቲቻ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን የአካባቢው ማህበረሰብ ሕይወት እንዲለወጥ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመድረኩ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተጨማሪ ግብዓቶችና ተሞክሮዎችን እንደሚያገኝም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም