ቀጥታ፡

ሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- ሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በርትተን ከሰራን፣ ጀምረን ከጨረስንና ክፍተቶችን እያየን መሙላት ከቻልን፣ ዘላቂና ተከታታይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ የኢትዮጵያን ብልፅግና በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ በሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኘውን "ጎበዝ ሶላር ሴል" ማምረቻንና ሌሎች ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በግል ባለሀብት የተገነባው ሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ከጅማና ከኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን፣ ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር ደግሞ በመጠን የሚስተካከል ነው።

የሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሠላሳ ሼዶች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፤ ስፋት ያለው፣ በርካታ ሰዎችን የሚይዝና ለከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ የግል ዘርፉ በኢንቨስትመንት መስክ ያለውን ሚና አጎልቶ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በጨርቃጨርቅ ላይ ተመስርቶ የነበረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርት አሁን ላይ እንዲሰፋ በተከናወነው ተግባር፤ ሶላር፣ የኤሌክትሪክ ባጃጅ፣ ጫማና አልባሳትን የመሳሰሉ ምርቶች በኢኮኖሚ ዞኑ እንደሚመረቱ ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ ዞኑ ባሉ ሼዶች የተለያዩ ምርቶች መመረታቸው የገበያ ዕድልን የሚያሰፋ መሆኑንም አንስተዋል።

በኢኮኖሚ ዞኑ ያለው "ጎበዝ ሶላር ሴል" ማምረቻ አሁን ላይ ሁለት ጊጋ ዋት እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ዓመት ተጨማሪ ሁለት ጊጋ ዋት ማምረት ይጀምራል ብለዋል።

የሶላር ሴል ምርት በአጭር ጊዜ ውስጥ መመረት የጀመረና አሁን ላይ እየሰፋ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በአዲስ አበባ የሚገኝና በርካታ ሼዶች ያሉት በመሆኑ፣ በርካታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ዕድል ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢነርጂና ለአገልግሎት ዘርፍ ዕድገት የሚውል በመሆኑ፣ በበርካታ መንገዶች በኢኮኖሚው ላይ አስተዋፅኦ የሚያበረክት እንደሆነም ገልፀዋል።

ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለእውቀት ሽግግርና ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች የሚውል በመሆኑ፣ ጥቅሙን አሟጦ ለመጠቀም የተሳካውንና የሚቀረውን በመለየት በትኩረት መሥራት እንደሚጠይቅ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራዊ ለውጥ እያስመዘገበና የኢንዱስትሪ ሽግሽግን እያመጣ ያለ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህን ማጠናከር ከተቻለ በቀጣዮቹ ዓመታት ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ራሷን የመቻል ዕድል እንዳላት የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የመጣውን ውጤት በማስፋትና በማሳደግ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ ከሁሉም የሚጠበቅ ዐቢይ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም