ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት እየሠሩ መሆናቸውን ሲቪክ ማኅበራት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት እየሠሩ መሆናቸውን ሲቪክ ማኅበራት ገለጹ
መቱ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጠት እየሠሩ መሆናቸውን በኢሉአባቦር ዞን የሚገኙ የሲቪክ ማኅበራት ገለፁ።
የኢሉባቦር ዞን ሴቶች ማኀበር ሊቀ መንበር ወይዘሮ ዓባይነሽ ሙሉነህ እና የዞኑ ሴቶች ፌዴሬሽን ኃላፊ ሀገሬ ሀብታሙ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ በየደረጃው ላሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይ በሴት አደረጃጀቶች ውስጥ የታቀፉ ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የምርጫ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ምርጫው፤ ዴሞክራሲያ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጀመሩትን ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።
በሲቪክ ማኅበራቱ የተሰጣቸው ሥልጠና በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ በቂ ግንዛቤ እንዳስያዛቸው የተናገሩት ደግሞ የመቱ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ናሐዊ ደፋር ናቸው።
በአሁኑ ወቅትም በምርጫ ታዛቢነት መመረጣቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን የሕዝብ አደራ በአግባቡ ለመወጣት ሥልጠናው ዐቅም እንደሆናቸው ነው የሚገልጹት።
ሌላኛዋ የወረዳው ነዋሪ ሙና ኢሳ፤ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊነቱ የተረጋገጠ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሲቪክ ማኅበራቱ እያከናወኑ ያለው ተግባራት መቀጠል ይገባዋል ይላሉ።
ማኅበራቱ ባዘጋጁት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ በመሳተፍም፤ በምርጫው ወቅት በታዛቢነት ለመቀመጥ መመረጣቸውን ነው ያመለከቱት።