ቀጥታ፡

ለግብርና ኢንቨስትመንት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የዘርፉ ውጤታማነት እያደገ ነው

ቦንጋ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ ለግብርና ኢንቨስትመንት የተፈጠረ ምቹ ሁኔታ የዘርፉን ውጤታማነት እንዳሳደገው ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በቦንጋ ከተማ መክሯል።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ደረጀ አበበ እንደገለጹት መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የግል ባለሀብቱን ለማበረታታት የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ቀርፆ ተግባራዊ አድርጓል።


 

ለዚህም ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻል ለግል ባለሀብቱ በርካታ ማበረታቻዎችን በማድረግ  ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

የግብርና ኢንቨስትመንት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

ባለሀብቶች በገቡት ውልና በፖሊሲው በተቀመጠው መሰረት የወሰዱትን መሬት በአግባቡ ማልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በሰፊው መስራት እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በትኩረት እንዲሰሩም አሳስበዋል።

የመድረኩ ዓላማም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ችግር ለይቶ መፍትሄ ማበጀት፣ ትልልቅ የምግብ ዘይት አምራቾች በእርሻ ዘርፍ እንዲሳተፉ ማድረግና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በመምከር ዘርፉን ይበልጥ ማጠናከር መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ግብርና ለሀገር ኢኮኖሚ ያለዉ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አስራት አስፋ ናቸው።

ባለፉት ጊዜያት በዘርፉ በተሰሩ ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ባለሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ከፋይናንስ አቅርቦት ጀምሮ በርካታ ድጋፎች በተሻለ መልኩ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ በተሰጠ ትኩረት 544 ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ መሰማራታቸውንና የዘርፉ  ፍሰት በከፍተኛ  ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች 177ሺህ ሄክታር መሬት መመቻቸቱንና የህግና የአሰራር ማእቀፎች መዘጋጀታቸውን  ተናግረዋል።


 

በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተሰራው ስራ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትልና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሀላፊ ከበደ ተስፋዬ ናቸው።

ባለሀብቶቹ በቡና፣ በሰብል፣ በሻይ ልማት እንዲሁም በቅባት እህሎችና በሌሎች የግብርና ልማት ስራዎች መሰማራታቸውን አንስተው፣ ከእነዚህም ውስጥ 93ቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ስራ የገቡ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም