ቀጥታ፡

አስተዳደሩ ያስገነባው ሕንጻ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል- ከንቲባ ጥራቱ በየነ

ሐዋሳ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በሐዋሳ ከተማ ያስገነባው ሕንጻ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ።

ከንቲባው የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በሐዋሳ ከተማ ያስገነባውን ባለ ስምንት ወለል ሕንጻ ዛሬ መርቀዋል።

በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ዓመታት በተደረገ ሪፎርም ተቋሙ አስደናቂ ለውጥ ማስመዝገቡን አንስተዋል።

ማኅበራዊ ዋስትናን ከማረጋጋጥ ባለፈ ሀብት መፍጠር በሚችል የኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ በመግባት ያስመዘገበው ውጤት ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ ይሆናልም ብለዋል።

ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ሕንጻው፤ ለሐዋሳ ከተማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተጨማሪ ዐቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።


 

ሕንጻው ለቢሮ አገልግሎት፣ ለካፌና ሬስቶራንት፣ ለሕክምና መስጫ ማዕከላትና ለተለያዩ የንግድ አገልግሎቶች እንዲውል ጭምር ተደርጎ መሠራቱን የተናገሩት ደግሞ በመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የደቡብ ሪጅን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተሾመ ባብሳ ናቸው፡፡

የግንባታ ሥራው በ2015 ዓ.ም መጀመሩንና ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም