ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ኢትዮጵያ ሳይንሳዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት መሰረት ጥሏል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ኢትዮጵያ ሳይንሳዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት መሰረት መጣሉን የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሶሳይቲው የበላይ ጠባቂ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2004 የተመሰረተው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ 21ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ሳይንሳዊ ትውልድ ትገነባለች የሚለውን መርህ ገቢራዊ ለማድረግ በምታደረገው እንቅስቃሴ ሶሳይቲው ጉልህ ሚና በመወጣት ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲና በመንግስት ቁርጠኝነት ለሳይንስ ዕድገት ወሳኝ የሆኑ እንደ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማት በተደራጀ መንገድ እንዲቋቋሙ ተደርጓል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ወጣት የሳይንስ ተመራማሪዎችና አስትሮኖመሮችን ማፍራቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በርካታ ወጣቶችን በማፍራትና በምርምር ተስፋ ሰጪ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ ከዚህ በላይ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ሳይንስ ለግብርና የዲጂታል አብዮት እድገትና ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር እኩል ለመራመድ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ዘመኑን የሚዋጅ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ወጣቶችን በሳይንስና አስትሮኖሚ ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት በማጠናከር በዘርፉ ከመጠቁ ሀገራት ጋር ያለውን ልዩነት ማጥበብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተወሰኑ ስራዎችና ውጤቶች መርካት የለብንም ያሉት አቶ ደመቀ፤ ለዚህ ደግሞ የወጣቶች ተሳትፎ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ለስፔስ ሳይንስ ዕድገት ትልቅ ባለውለታ መሆኑን አስታውቀዋል።

ስፔስ ሳይንስ የሉዓላዊነት፣ የምግብ ዋስትና፣ የዲፕሎማሲ፣ የጤና፣ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት፤ ያለ ስፔስ ሳይንስ መቆም እንደማይቻል ገልጸዋል።

የሀገርን ኢኮኖሚና ኅልውና ለማስቀጠል ስፔስ ሳይንስ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፤ ሶሳይቲው ወጣቶችን ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት የተለያዩ ተቋማት መደገፍና በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም