ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል የመሆን ጉዞዋን አጠናክራ ቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአህጉሪቱ የታዳሽ ኃይል ልማት ማዕከልነቷን ለማረጋገጥ በጀመረችው ጉዞ ያስመዘገበቻቸውን ተጨባጭ ውጤቶች አጠናክራ መቀጠሏን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።  


 

ኢትዮጵያ በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም፣ የአፍሪካ ህብረትን የ2063 አጀንዳ ለማሳካትና አህጉሪቱን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች። 

አሁን ላይ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉት የቀጣናው የኃይል ሽያጭ ስምምነቶችም፣ ሀገሪቱ የጀመረችው የብልፅግና ጉዞ በተጨባጭ ውጤት የታጀበ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የአይሻ 2 እና የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች በስኬት ተጠናቅቀው ወደ ሥራ በመግባታቸው የሀገሪቱ የኃይል ማምረት አቅም ከ9 ሺህ 752 ሜጋ ዋት በላይ ደርሷል። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል መረጃ እንደሚያሳየው በ2018 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 24 ሺህ 970 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለሀገር ውስጥና ለጎረቤት ሀገራት ለሽያጭ ቀርቧል።

በበጀት ዓመቱ ለውጭ ሀገራት እና ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከቀረበ የኃይል ሽያጭ 366 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል።  

ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ138 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ብልጫ እንዳለው ነው የተመለከተው።


 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ የኤሌትሪክ ኃይል የምታመነጨው ከውኃ፣ ከንፋስ ኃይል፣ ከፀሐይ ሐይል እና ከጂኦተርማል ነው። 

የኃይል አማራጭን ይበልጥ በማስፋት በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኃይል አቅርቦት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘችው ርዕይ በተጨባጭ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተፈጠረው የኢነርጂ መሠረተ ልማት ትስስር እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያና ከታንዛኒያ ጋር የኃይል ሽያጭ ግንኙነት መጀመሩን ጠቅሰው፤ ይህም የሀገሪቱን በጋራ መልማት የሚለውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እውን ከማድረግ ባለፈ በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል። 


 

ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የአጀንዳ 2063 የመሰረተ ልማት ትስስር ግቦችን ለማሳካት ያላትን ግንባር ቀደም መሪነትና አስተዋጽኦ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ከኃይል ሽያጭ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለኃይል መሰረተ ልማቶች መስፋፋትና ጥገና ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ለአብነትም የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ወጪ በሀገር ውስጥ የፋይናንስ አቅም መሸፈኑን ጠቅሰው፤ ይህም የኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግና ከብክለት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም ሆኗል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ የኃይል ሽያጭ ግቧን ከጎረቤት ሀገራት ባለፈ እስከ ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ድረስ የማድረስ ሰፊ ዕቅድ ይዛ እየሰራች መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

በአሁኑ ወቅት ደቡብ ሱዳን የኃይል ፍላጎት በማሳየቷ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ በባለሙያዎች ደረጃ ዝርዝር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በተመሳሳይ ሶማሊያ የኃይል ፍላጎት እንዳላት የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የሌሎች ሀገራትን የኃይል መስመር በመጠቀም ድንበር ለማይጋሩ ሀገራት ጭምር ኃይል ለማቅረብ ዕቅድ መኖሩን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም