ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን እየፈፀመው ያለው ግፍ የህዝብ ጠላት ሆኖ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው -የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን እየፈፀመው ያለው ግፍ የህዝብ ጠላት ሆኖ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው -የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር
ሰቆጣ፤ ሚያዚያ 24/2018(ኢዜአ)፦ ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን እየፈፀመው ያለው ግፍ የህዝብ ጠላት ሆኖ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው ሲል የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አስታውቋል።
ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ ከተማ በዛሬው እለት ተካሂዷል።
የብሄረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን እንዳሉት፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለአካባቢው ሰላምን ያስገኝ ነበር።
ይሁን እንጅ ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ስምምነቱን በመጣስ በአካባቢው ዳግም ወረራ በማካሄድ እና ህዝቡን በማፈናቀል ለችግር እንዲጋለጥ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት በብሄረሰብ አስተዳደሩ በሚገኙት የአበርገሌና ፃግብጅ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ግፍና መከራ እያደረሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
"ቡድኑ በቅርቡ በአበርገሌ ወረዳ የፈፀመው ወረራ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነትን በግላጭ እንደተጣሰ ማሳያ ነው" ያሉት አቶ ሹመት ህዝቡን በማፈናቀል ዝርፊያ እየፈፀመ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህ እኩይ ድርጊት በመጭው ግንቦት 24 የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ ታልሞ እየተሰራ መሆኑን በመገንዘብ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ቡድኑን ማውገዙ ተገቢነት ያለው እንደሆነም ተናግረዋል።
የሰቆጣ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ በበኩላቸው፤ ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን በሚፈፅመው ግፍ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ህፃናትም ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል ብለዋል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነትን በመጣስ በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ ለሰላም ደንታ እንደሌለው ማሳያ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብና አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ ነው የጠየቁት።
በሰቆጣ ከተማ በዛሬው እለት የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ተላላኪዎች ጠቅላላ ምርጫውን ለማደናቀፍ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተገንዝበናል ነው ያሉት።
በዚህም ፀረ ህዝብ ተግባራቸውን በይፋ እየተገበሩ ነው ሲሉም በሰልፉ ወቅት ተደምጠዋል።
ወረራና ዘረፋው ለዋግ ኽምራ ህዝብና ለኢትዮጵያ ሰላም እንቅፋት በመሆኑ መንግስት የህግ ማስከበር ስራን ሊያከናውን ይገባል ሲሉም ጠቅሰዋል።
ዛሬ ማለዳ በተካሔደው ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎችና ከወረዳዎች ተፈናቅለው በአካባቢው የተጠለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።