የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ በመላው ሀገሪቱ በስፋት እየተከናወነ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ ማስቻሉን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመቅረፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ይፋ የተደረገ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
ይህ የልማት ዕቅድ በዋናነት የወተት፣ የዶሮ፣ የማር፣ የሥጋ እና የዓሣ ሀብት ልማትን በቤተሰብ ደረጃ በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ነው።
በገጠርና በከተሞች በስፋት እየተተገበረ የሚገኘው ንቅናቄው የዜጎችን የምግብ አጠቃቀም ባህል በመቀየርና ራስን በምግብ ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በማፋጠን ረገድ እንደ ዋና የልማት ምሰሶ ተደርጎ ይወሰዳል።
ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች በአግባቡ መጠቀም ከቻለችና ካለማች፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች የቅንጦት ምግቦች ሳይሆኑ ከሌማት መጥፋት የሌለባቸው እንደሆነ ታምኖበት በስፋት እየተሰራ ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ አዚዝ አያሌው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሌማት ትሩፋት እየተከናወኑ የሚገኙት ተግባራት በምግብ ራስን ለመቻል የሚያግዙ ናቸው።
የሌማት ትሩፋት ተግባራቱ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስቻይ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በወተት፣ በዶሮ፣ በማርና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ምርቶችን በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል መፈጠሩንና የህብረተሰቡ ገቢ እንዲጨምር ብሎም የሀገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በእንቁላል፣ በወተትና በስጋ ምርት ኢትዮጵያ ቀድማ የጀመረችው እንቅስቃሴ አሁን ያለውን የዓለም የገበያ ቀውስ ለማረጋጋት ትልቅ አቅም መፍጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት ምርታማነት ቀጣይነት እንዲኖረው የባለሀብቱ ተሳትፎ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፤ ባለሀብቱ በዘርፉ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች በበኩላቸው፤ በሌማት ትሩፋት በመሰማራት ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የተሻለ ገቢ እንዲኖራቸው እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።
አስተያየታቸውን ከሰጡ መካከል የተካልኝ ከበደ እና ጓደኞቻቸው ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ተካልኝ አየለ፤ በሌማት ትሩፋት ዘርፍ በመሰማራት ተጨባጭ ውጤት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሥራው በርካታ ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ከእንስሳቱ በሚያገኟቸው ምርቶች ከራሳቸው ባለፈ የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ወጣቶች በዘርፉ በመሰማራት የተሻለ ገቢ እንዲኖራቸውና ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ዘመኑ ታረቀኝ እና ወይዘሮ ጸዳለ እሸቴ፤ በሌማት ትሩፋት የሚያገኙት ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ከራሳቸው የዕለት ገበታ ባለፈ ለሌሎች በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።