የተመቻቸውን ዕድል በመጠቀም የመራጭነት ካርድ ወስደናል - የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የተመቻቸውን ዕድል በመጠቀም የመራጭነት ካርድ ወስደናል - የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች
አሶሳ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያመቻቸውን ዕድል በመጠቀም የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።
ቦርዱ የምርጫ ካርድ ላልወሰዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በካምፕ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በልዩ ሁኔታ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ የመራጮች ምዝገባ እያካሄደ ነው።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ባገኙት የመራጭነት ዕድል ድምጽ ለመስጠት የሚያበቃቸውን የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ መልካሙ መላኩ እንደገለጸው፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለሀገር ግንባታ፣ ለሰላም እና ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ፓርቲ እንዲመርጡ ዕድል መመቻቸቱ የሚበረታታ ነው።
ተማሪዎች ባሉበት ሆነው በቴክኖሎጂ ታግዘው መመዝገብ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት የታየ ትልቅ መሻሻል መሆኑን ጠቁሟል።
ተማሪ አበባ የኛነው በበኩሏ፤ ተማሪዎች በምርጫው እንድንሳተፍ መደረጉ የመምረጥ መብታችንን ተጠቅመን ሀገርን በልማትና በሰላም ግንባታ ወደፊት የሚያራምድ ፓርቲ ለመምረጥ ዕድል ይሰጠናል ብላለች።
ለተማሪዎች የተመቻቸውን ዕድል በመጠቀም የምርጫ ካርድ መውሰዱን የገለጸው ተማሪ አቢያን ኩኩ፤ ባሉበት ሆነው ካርድ ማውጣት መቻላቸው ጊዜና ጉልበት በመቆጠቡ ሊበረታታ ይገባል ብሏል።
ግንቦት 24 ቀን 2018 በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ድምጹን ለሚፈልገው የፖለቲካ ፓርቲ በመስጠት የዜግነት ኃላፊነቱን ለመወጣት መዘጋጀቱንም አረጋግጧል።