ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት ዘላቂ ተጠቃሚነታችን እንድናረጋግጥ አግዞናል - የመርሐ-ግብሩ ተሳታፊዎች

ገንዳውኃ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር መሳተፋቸው ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዳስቻላቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ ዜጎች ተናገሩ።

የመተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሙሉ መርሻ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ ከ2 ዓመት በፊት በ400 ሺህ ብር የጀመረውን የወተት ልማት ካፒታል አሁን ወደ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር አሳድጓል።

ከ16 ላሞች የሚያገኘውን የወተት ምርትም ለገበያ በማቅረብ ዘላቂ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግሯል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በመታቀፍ በአምስት በሬዎች የጀመረውን የማድለብ ሥራ ይህን አሃዝ ወደ 15 ማሳደጉን የገለጸው ደግሞ የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪ ወጣት ቢትወደድ አዳነ ነው።

በዚህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጡን ጠቁሞ፤ ለውጤታማነቱም የባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስታውቋል።
 



በዶሮ ዕርባታ ሥራ በመሰማራት ከእንቁላል ሽያጭ ብቻ በወር እስከ 25 ሺህ ብር እንደሚያገኙ የገለጹት ደግሞ በከተማዋ በዘርፉ የተሰማሩት አስቴር ገበየሁ ናቸው።

በወተት ልማት ዘርፍ ለመሰማርት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።


 

የምዕራብ ጎንደር ዞን እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ እያያው ታከለ እንዳሉት፤ ወጣቶችን በዘርፉ በማደራጀትና በግል ወደ ሥራ እንዲገቡ በስፋት እየተሠራ ነው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ3 ሺህ 900 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች 203 ሺህ የሚጠጉ በሬዎችን አድልበው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም