ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሚገኘውን የ“ጎበዝ ሶላር ሴል” ማምረቻን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፦‎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ በሁዋጂያን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኘውን የ“ጎበዝ ሶላር ሴል” ማምረቻን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፋብሪካው በ2025 የኢንቨስትመንት ፎረም (Invest in Ethiopia Forum) አማካኝነት በተፈረመው ስምምነት መነሻ በ100 ሚሊየን ዶላር የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ የተቋቋመ መሆኑን አውስተዋል።

በውጤታማ ድጋፍ እና ክትትል በስድስት ወራት ብቻ እውን የሆነው "ጎበዝ ሶላር ሴል" ማምረቻ ዘመናዊ ማሽኖች እና በቴክኖሎጂ የተዋቀረ ነው ብለዋል።

ማምረቻው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልም መፍጠር መቻሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።


 

በመጀመሪያ ምዕራፍ 2 ጌጋዋት ዓመታዊ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው፣ የኢትዮጵያን የኃይል ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ ኃይል ለማድረግ የተጀመረውን ሀገራዊ ርዕይ እውን ለማድረግ ተደማሪ አቅም መፍጠሩን ነው ያብራሩት።


 

በዚሁ የኢንደስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኘውን የጫማ ማምረቻ እና ንዑስ የኤሌክትሪክ ጣቢያን መመልከታቸውንም በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም