ቀጥታ፡

የሚበጀንን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን ዕለት እየጠበቅን ነው - የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች

ሰመራ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በሆነው ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለሀገር ግንባታ የሚበጅ ፖሊሲ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢዜአ በሰመራ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት፤ በምርጫ ካርዳቸው የተሻለ ሐሳብ አለው፣ ሀገርና ሕዝብንም ወደፊት ያራምዳል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።


 

አቶ ዘይኑ ሙሳ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ምርጫ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፤ ለሕዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትና ዘላቂ ሰላም አበክሮ ይሠራል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

ፓርቲዎች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮችና ቋንቋዎች ሐሳባቸውን ለሕዝብ እንዲያቀርቡ መደረጉ እንደ መራጭ በቂ ግንዛቤ ለመያዝ እንዳስቻላቸው አስረድተዋል።

ምርጫ ይበጀኛል ብለን ድምጻችንን ለምንፈልገው የፖለቲካ ፓርቲ የምንሰጥበት በመሆኑ ሁሉም ሰው ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም መዘጋጀት አለበት ያሉት ደግሞ አቶ ሙሳ አብዱ ናቸው።

የምርጫውን ቀን እየጠበቁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለሰላምና ልማት መቀጠል የተሻለ ሐሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
 



አቶ መሐመድ ይመር በበኩላቸው፤ የፓርቲዎችን አማራጭ ሐሳቦች ሕብረተሰቡ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲያገኝ መደረጉ የተሻለ ሐሳብ ያለውን ፓርቲ ለመለየት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

የምርጫ ካርዳቸውን በወቅቱ ወስደው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ድምጻቸውን ለመስጠት መጪውን ግንቦት 24 እየጠበቁ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም