ቀጥታ፡

የኮሪደርና ግዙፍ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2018 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደርና ግዙፍ የልማት ሥራዎች ገጽታዋን በመቀየር ረገድ አስደናቂ ለውጥ ማሳየታቸውን የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓቲካ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ተሠርቶ የታየው ለውጥ ለማመን የሚከብድ ሥራ ነው።


 

አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ በተሠራው ሥራ ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎች፣ ለእግር ጉዞ የሚሆኑ ውብ ስፍራዎችና ፓርኮች ያሏት ዘመናዊ ከተማ ሆናለች ብለዋል። 

ይህ ሥራ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሕዝብም ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጀምሮ በቱሪዝም ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት አድናቆት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር አሌሃንድሮ ኢቭስ እስቲቪሊ ካስትሮ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ የላቀ ውበት ከመስጠቱም በላይ ለሕዝቡ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ መመልከታቸውን ተናግረዋል።


 

በከተማዋ ውስጥ ለመዘዋወር፣ ለማሽከርከር እና ለመዝናናት አሁን ያለው ሁኔታ ቀላል እና ማራኪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ በበኩላቸው፤ በቆይታቸው ወቅት የተመለከቱት የኮሪደር፣ የፓርኮች እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች አስገራሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። 


 

በከተማዋ የተሠሩት ሥራዎች እጅግ አስደናቂ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከተማዋ ለመኖርም ሆነ ለመዝናኛ ተመራጭ እንድትሆን እያደረጋት ነው ብለዋል።

ለውጡ የታየበትን ፍጥነት አስደናቂ ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ኤር ቫይስ ማርሻል ሲትዋት ናዪማ ናቸው።


 

ከተማዋን ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ እጅግ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም