ብልፅግና ፓርቲ የህብረተሰቡን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን የበለጠ ያከናውናል - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ የህብረተሰቡን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን የበለጠ ያከናውናል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2018(ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ የህብረተሰቡን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን የበለጠ እንደሚያከናውን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅስቀሳ በአዲስ አበባ ስታድየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመርሀግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አዳነች አቤቤ፣ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሞገስ ባልቻ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ ፓርቲውን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎች፣ የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ህዝብ ብቸኛው የስልጣን ባለቤት ነው።
ያለ ህዝብ ተሳትፎና አጋርነት ብልፅግናን እውን ማድረግ እንደማይቻልም ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት ማከናወናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያቆመው አንዳች ምድራዊ ሀይል እንደሌለ ገልጸዋል።
በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ማንንም ያልዘነጉ አካታች መሆናቸውን ጠቁመው፤ እነዚህ ተግባራት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
ብልፅግና ቃሉን የሚጠብቅ ፓርቲ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ የከተማዋን ገጽታም ቃል በገባው መሰረት መገንባቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ብልፅግና ፓርቲ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ቃል በመግባት "ብልፅግናን ምረጡ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።